ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካው የወንዶች ስካውት ማኅበር የፆታዊ ጥቃት ክሶች ቀረቡበት
100 ሺህ ያህል ፆታዊ ጥቃት ደርሶብናል የሚሉ የአሜሪካ የወንድ ስካውት አባላት ለአገሪቱ ቦይ ስካውትስ ማኅበር ክስ ማቅረባቸው ተነገረ።
ተጠቂዎቹ የአሜሪካ ቦይ ስካውትስ የተሰኘው የታዳጊ ወንዶች ማኅበር ውስጥ ሳሉ በርካታ ፆታዊ ጥቃት ስለደረሰባቸው ካሳ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
የተጠቂዎቹ ጠበቃ ድርጊቱ በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ የፆታዊ ጥቃት የክስ መዝገብ ነው ብሎታል።
ተጠቂዎቹ ክስ የከፈቱት እስከ ባለፈው ሰኞ ድረስ በተሰጠው ቀነ ገደብ መሠረት ነው።
በፈረንጆቹ 2012 ይፋ የተደረገ አንድ ውስጣዊ መረጃ ማኅበሩ ውስጥ ለዓመታት ፆታዊ ጥቃቶች ሲፈፀሙ እንደነበር አመልክቷል።
በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መባቻ ማኅበሩ ኪሳራ ደርሶብኛል ሲል ለመንግሥት ያሳወቀ ሲሆን፤ አባላቱ ላይ ለደረሰው በደል ይቅርታ ጠይቋል።
በማኅበሩ፤ በተጠቂዎቹ እና በአክሲዮን ማኅበራት መካከል ድርድር እንደሚጀመር ታውቋል።
ማኅበሩ አሁንም በርካታ አባለት አሉት። አሁን ባለው መረጃ ዕድሜያቸው ከአምስት ጀምሮ እስከ 21 ድረስ ያሉ ሁለት ሚሊዮን ታዳጊ ወንዶች የስካውት ማኅበሩ አባላት ናቸው።
ነገር ግን ማኅበሩ በ1970ዎቹ ከዚህ እጥፍ የሚሆኑ አባላት ነበሩት።
የአሜሪካ ፌዴራል ፍርድ ቤት የማኅበሩን መክሰር ተመልክቶ ለተጠቂዎች ከሳ ሊከፍል ይችላል።
የአሜሪካ የካቶሊክ ቤተክርስትያንም ተመሳሳይ ታዳጊ ወንዶች ላይ የሚደርስ የፆታዊ ጥቃት ክስ ይቀርብባታል።
ጠበቃ ፖል ሞሰስ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ይህ በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ የፆታዊ ጥቃት ክስ ነው።"
ማኅበሩ የደረሰባቸውን ፆታዊ ጥቃት ይፋ ለማድረግ ደፈረው የወጡ አባላቱን 'ድፍረት' አድንቋል።
በፈረንጆቹ 2012 ሎስ አንጀሊስ ታይምስ ጋዜጣ 5 ሺህ ያህል ክሶች ስካውት ማስተር የሚባሉ ግለሰቦች ላይ መመሥረታቸውን ይፋ የሚያደርግ መዝገብ አጋልጦ ነበር።
ስካውት ማስተሮች የማኅበራት መሪዎች ሲሆኑ በየግዛቱ ያሉ የማኅበሩ አባላትን የሚያንቀሳቅሱ ናቸው።
በርካታ ክሶች ለፖሊስ ሪፖርት እየተደረጉ አይደሉም ተብሏል።
ጠበቃ ሞሰስ በ2012 ፆታዊ ጥቃት የደረሰበት አንድ ታዳጊን ወክለው የ20 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ረትተዋል።