አትሌት ካስተር ሰሜንያ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ይግባኝ ልትጠይቅ ነው

ካስተር ሴሜንያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ስመጥሯ ደቡብ አፍሪካዊት አትሌት ካስተር ሰሜንያ በሴት አትሌቶች ሰውነት ሊገኝ የሚገባውን የቴስቴስትሮን ሆርሞን መጠን የሚገድበውን የዓለም አትሌቲክስ ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ልትጠይቅ ነው።

ጉዳዩንም ወደ አውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ ብላለች።

በ800 ሜትር ሁለት ጊዜ ኦሊምፒክን ማሸነፍ የቻለችው የ29 ዓመቷ አትሌት ከዚህ ቀደም ውሳኔውን በመቃወም ሁለት ጊዜ ይግባኝ ብትጠይቅም ጉዳይዋ ውድቅ ተደርጓል።

ይግባኟንም ያስገባችው ለዓለም አቀፉ የስፖርት ግልልግል ፍርድ ቤት እንዲሁም የስዊዘርላንድ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነበር።

በዚህም ሕግ መሰረት አትሌቷ ከ400 ሜትር -1.6 ኪሎሜትር ርቀት ባለው ውድድር መሳተፍ ከፈለገች በሰውነቷ ውስጥ ያለውን የቴስቴስትሮን መጠንን የሚቀንስ መድኃኒት መውሰድ ይጠበቅባታል።

በደቡብ አፍሪካ የአትሌቷ ጠበቃ ደንበኛቸው ይህንን ውሳኔ በፀጋ እንደማትቀበለውና ይግባኝ ትጠይቃለች ብለዋል።

"የዓለም አትሌቲክስ ሕጎች ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ እየሄዱ ነው" ያሉት የአትሌቷ ጠበቃ የሕግ ባለሙያው ግሬግ ኖት ናቸው።

እኩል የሆነች ዓለምን ለመፍጠርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን የሰብዓዊ መብት እሴቶች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ በርካቶችም በማኅበራዊ ሚዲያ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ዋናው ተቆጣጣሪ ባለፈው ዓመት ነው የተለየ 'ሴክሹዋል ዴቨሎፕመንት' (የተለየ ፆታዊ ባህርይ) የሚያሳዩ አትሌቶች ከ400ሜትር -1.6 ኪሎሜትር ርቀት ባለው መወዳደር ከፈለጉ መድኃኒት እንዲወስዱ ያስገደደው። ካለበለዚያ የሚወዳደሩበትን ርቀት መቀየር ይገባቸዋል ብሏል።

አትሌቶች በተፈጥሮ ከፍተኛ የቴስቴስትሮን መጠን ካላቸው በውድድሩ የበለጠ ተጠቃሚነት ይኖራቸዋል ብሎ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ያምናል።

አትሌቷ በሁለት ፍርድ ቤቶች ያቀረበችው ይግባኝ ውድቅ መደረጉንም ተከትሎ የዓለም አትሌቲክስ መመሪያው ተግባራዊ ይሆናል ብሏል።

ልትጠይቀው ያሰበችው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ ማለት በጎሮጎሳውያኑ 2012 እና 2016 የኦሊምፒክስ ወርቅ ባለቤት የሆነችው ካስተር ሰሜንያ በቶክዮ በሚደረገው ውድድር ላይ ተሳታፊ አትሆንም።

አትሌቷ በ200 ሜትር ተሳታፊ እንደምትሆን ያሳወቀች ሲሆን ይህም ርቀት መድኃኒት መውሰድ አይጠበቅባትም።