በኢራቅ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ አልባ ይሆናሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኢራቅ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚቆየዩባቸው በርካታ ካምፖች በፍጥነት እየተዘጉ መሆኑን ተከትሎ እስከ 100 ሺ የሚደርሱ ሰዎች መጠለያ አልባ ሊሆኑ እንደሚችሉ የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት አሳሰበ።
የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል እንደሚለው የኮሮረናቫይረስ ዓለምን እንዲህ እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያለ ቅድም ማስጠንቀቂያ እንዲወጡ እየተደረጉ ነው።
የኢራቅ መንግስት ወደመጡበት አካባቢ እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል።
ነገር ግን የአብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች መኖሪያ ቤቶች ከኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ጋር በሚደረገው ጦርነት ምክንያት የፈራረሰ ሲሆን እስካሁንም ድረስ ተመልሰው አልተገነቡም።
ከስድስት ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ኢራቃውያን በግጭቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን ጦርነቱ ከጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በርካቶች ተጎድተዋል።
በአሁኑ ሰአት ደግሞ 1.3 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች መጠለያ አልባ ናቸው። 4.7 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የተመለሱ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
የኢራቅ መንግስት በግድ መጠለያ ካምፖችን መዝጋት የጀመረው እኤአ ከ2019 ጀምሮ ነው።
ምንም እንኳን ወደ ካምፖቹ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እየቀነሰ ቢሆንም የኢራቅ መንግስት አሁንም ቢሆን ማቆያዎቹን መዝጋት እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የኖርዌይ ስደተኞች ካውንስል ዛሬ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁኔታው በእጅጉ እንዳሳሰበውና በባግዳድ፣ ዲያላ፣ ካርባላ፣ አንባር፣ ሱላይማኒያ፣ ኪርኩክ እና ኒኔቫህ ውስጥ የሚገኙ መጠለያዎች ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል አስታውቋል።
ካውንስሉ አክሎም የኢራቅ መንግስት ሌላው ቢቀር ካምፖቹን ከመዝጋቱ በፊት ለቤተሰቦች ቀደም ብሎ እንዲያሳውቅና ቢያንስ አንድ ወር መዘጋጃ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።












