ሕንዳውያን የስኳር ምርት ስለተትረፈረፈ አብዝተው እንዲጠቀሙ ተነግሯቸዋል

ሕዝቧ ስኳር አብዝቶ እንዲጠቀም እየመከረች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሕንድ በጣም የበዛ ስኳር በማምረቷ ሕዝቧ ስኳር አብዝቶ እንዲጠቀም እየመከረች ነው።

የሕንድ ስኳር ምርት ማሕበር ስኳር ጤና ላይ ጉዳት ያመጣል የሚባለውን ችላ ብለው ሰዎች አብዝተው እንዲጠቀሙ መክሯል።

ሕንዳውያን በአማካይ በዓመት 19 ኪሎ ግራም ስኳር ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ ከተቀረው ዓለም ሲነፃፀር አነስተኛ ነው።

ቢሆንም ሕንድ ካላት ሕዝብ አንፃር ከፍተኛ ስኳር ተጠቃሚዋ ሃገር ናት።

የሕንድ የስኳር ምርት መጠን በዚህ ዓመት በ13 በመቶ አድጎ 31 ሚሊዮን ቶን ምርት እንደሚመረት ይጠበቃል።

ነገር ግን መንግሥት እንደ ሌላ ጊዜው በገፍ ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ትቶ ለሕዝብ ሊያከፋፍል ይችላል ተብሏል።

የስኳር ምርት ማሕበሩ ድረ-ገፁ ላይ ስኳር መጠቀም እንደማይጎዳ የሚጠቁም ማስታወቂያ ለቋል።

ማሕበሩ ሰዎች ለሚሰሯቸው ምግቦች ሌላ ዓይነት ማጣፈጫ ከሚጠቀሙ ስኳር ቢጠቀሙ የተሻለ እንደሆነ የሚጠቁሙ ማስታወቂያዎች እየለቀቀ ነው።

የሕንድ የምግብ ሚኒስቴር ሱዳንሹ ፓንዴይ የሕንድ ማሕበረሰብ ለስኳር ያለው አስተሳሰብ የተዛባ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

እርግጥ ነው በሌሎች ሃገራት ሰዎች የስኳር አጠቃቀማቸውን እንዲያስተካክሉና ቀነስ እንዲያደርጉት ነው የሚመከሩት።

ስኳር ከመጠን ላለፈ ክብደትና በተለምዶ ስኳር በሽታ ተብሎ ለሚታወቀው ዳያቢቲስ ሊያጋልጥ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች።

የዓለም ጤና ድርጅት የተለያዩ ምግቦች ውስጥ፤ በተለይ ደግሞ ማርና የፍራፍሬ ጭማቂ ላይ የሚታከል ስኳር ለጤና አሳሳቢ ነው ይላል።

ሕንድ ውስጥ 50 ሚሊዮን ገደማ ገበሬዎች ሸንኮራ አገዳ ያመርታሉ። ሚሊዮኖች ደግሞ ስኳር በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው ይሠራሉ።

ሕንድ የተረፈ የስኳር ምርቷን ወደ ውጭ ለመላክ ማቀዷ በሌሎች ስኳር አምራች ሃገራት ዘንድ ቅራኔ ፈጥሯል።

ሌላኛው የተረፈ የስኳር ምርትን ማስወገጃ መንገድ ወደ ኢታኖል ቀይሮ መጠቀም ነው።

የሕንድ ስኳር ምርት ማሕበር የኢታኖል ምርት አሁን ካለው 1.9 ቢሊዮን ሊትር ምርት በሚቀጥለው ዓመት ወደ 3 ቢሊዮን ሊያድግ እንደሚችል ገምቷል።