በኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ እና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የነበረው የዕርቅ ሂደት መጠናቀቁ ተገለጸ

በቀሲስ በላይ መኮንን እና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የነበረው የዕርቅ ሂደት መጠናቀቁ ተገለጸ
ታትሟል

በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ መካከል እየተካሄደ የነበረው የዕርቅ ሂደት መጠናቀቁን ሂደቱን ሲመሩ የነበሩ ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንደሚያቋቁሙ መግለጻቸውን ተከትሎ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለፉት ጥቂት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ስታደርግ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ በቀሲስ በላይና በሲኖዶሱ መካከል ዕርቀ ሰላም ማውረድ እንደሆነ መዘገባችንም አይዘነጋም።

የዕርቅ ሂደቱን ሲመሩ የነበሩ አባቶች ዛሬ ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፤ "በመጀመሪያ ቋሚ ሲኖዶስ፣ በመቀጠልም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ባጸደቀው መሠረት የዕርቅ ሂደቱ ተጠናቋል" ተብሏል።

በመግለጫው ኦሮሚያ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መዳከም ያሳሰባቸው ወገኖች ችግሩን ለመፍታት በሚል የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለማቋቋም መወጠናቸውን በማስታወስ፤ "የተነሱት ችግሮች እንዳሉ በአባቶች፣ ሊቃውንትና ምእመናን ቢታመንም መፍትሔው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት መቋቋም ነው? የሚለው በአባቶች እና በምእመናን ዘንድ መከፋፈል ፈጥሯል" ይላል።

በኦሮሚያ አለ የሚባለውን የአገልግሎት መዳከም፣ በቋንቋው የሚያስተምሩ በቂ አገልጋዮች አለመኖር እና ሌሎችም የአስተዳደር ችግሮች እንዴት ይፈቱ? የሚለው ላይ ልዩነቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

ስለዚህም ችግሩን በውይይት ለመፍታት የተቋቋመው የሽማግሌዎች ቡድን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አመራሮችን፣ ቋሚ ሲኖዶሱን እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን እንዳነጋገረ በመግለጫው ተመልክቷል።

ላለፉት ስድስት ወራት ችግሩን ለመፍታት ውይይት ሲካሄድ እንደነበረም ተጠቅሷል።

"በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት መፍታት የተሻለ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ታምኖበታል" ሲልም መግለጫው ያትታል።

በኦሮሚያ ያጋጠመው የአገልግሎት መዳከም የመላዋ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ተደርጎ እንደሚወሰድ በመግለጽ "ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት በኦሮምኛ ቋንቋ የሚሰጠው አገልግሎት እጅግ በተጠናከረ መልኩ ለማካሄድ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች አንድ ሆነው እንዲነሱ አደራ እንላለን" ተብሏል።