በማሊ ራዲስን ብሉ ሆቴል ጥቃት ሁለት ሰዎች በሞት ተቀጡ

የማሊ ወታደሮች በራዲሰን ሆቴል አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የማሊ ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ2015 የውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን በመፈፀም በተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት አስተላለፈ፡፡

በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ባማኮ ውስጥ በሚገኝ የምሽት ክበብ እና በህዳር ወር ደግሞ ራዲሰን ብሉ ሆቴል ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ተገድለዋል፡፡

ከተከሳሾቹ አንዱ ጥቃቶች ላይ በመሳተፉ "ኩራት ይሰማኛል" ሲል ለፍርድ ቤቱ ገልጿል ፡፡

እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ ሠርጎ ገቦችን በመዋጋት ላይ ባለችው ሀገር ውስጥ ይህን መሰሉ የፍርድ ሂደት ያልተለመደ ነው ተብሏል፡፡

የፈረንሳይ ወታደሮች የሃገሪቱን ጦር ቢረዱም የማሊ መንግሥት ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልቻለም ፡፡

ሞሪታኒያዊው ታጣቂ ፋዋዝ ኡልድ አህሜይዳ የፈረንሳዩ ቻርሊ ሄብዶ መጽሔት የነቢዩ መሐመድን ካርቱን ምስል ማተሙን ለመበቀል በላ ቴራስ የምሽት ክበብ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጿል፡፡

ፋዋዝ ኦልድ አህመዲያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጥቃቱን ተከትሎ ሶስት ማሊያውያን፣ አንድ ፈረንሳዊ እና አንድ ቤልጄማዊ ተገድለዋል፡፡

የአህሜይዳ ማሊያዊ ተባባሪ ተከሳሽ ሳዱ ቻካ ለነበረው ተሳትፎ እሱም የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል ፡፡

አህሜይዳ የራዲሰን ብሉ ጥቃትን በማቀነባበርም ተከሷል ፡፡

ሁለት ታጣቂዎች ለዘጠኝ ሰዓታት 170 እንግዶችንና ሠራተኞችን አግተው የፀጥታ ኃይሎች ሕንጻውን ከመቆጣጠራቸው በፊት ቢያንስ 20ዎቹን ገድለዋል፡፡

ዘጠኝ ማሊያውያን፣ የሩስያ የበረራ ሠራተኞች፣ የቻይና የግንባታ ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የቤልጂየም ፖለቲከኛ እና አንድ አሜሪካዊ የእርዳታ ሠራተኛ ከተገደሉት መካከል ናቸው ፡፡

ሁለቱም ጥቃቶች ተከትሎ አል-ሙራቢቱን የተባለ አፍሪካ ጂሃዳዊ ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡