ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፖሊሶች የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ የአዕምሮ ህመምተኛ ያስነሳው ተቃውሞ
ፖሊስ አንድ ጥቁር አሜሪካዊን መግደሉን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ የሰዓት እላፊ አዋጅ በፊላደልፊያ ግዛት ተጥሏል።
ተቃውሞው ዘረፋ የተቀላቀለበትም ነው የተባለ ሲሆን ለሁለት ቀናትም ያህል በከፍተኛ ሁኔታም ተቀጣጥሏል።
የተገደለው አፍሪካዊ አሜሪካዊ ዋልተር ዋላስ ቤተሰቦች የአዕምሮ ጤና ህመም እንዳለበት ገልፀው ፖሊሶችም ተኩሰው ገድለውታል ብለዋል።
ፖሊስ በበኩሉ የያዘውን ቢላ አልጥልም በማለቱ ነው የተኮስነው ይላል።
በዚህ ሳምንት ማክሰኞም የፖሊስ ጭካኔን ሊቃወሙ በወጡ ሰልፈኞችና ፖሊስ መካከል ግጭት መፈጠሩ ተገልጿል። በከተማዋ ያሉትም የንግድ ተቋማትም ተዘርፈዋል ተብሏል።
የሰዓት እላፊ አዋጁ በመላው ከተማዋ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን ከምሽቱ ሶስት ሰዓትም ጀምሮ እንቅስቃሴ አይፈቀድም ተብሏል።
የፔኒሲልቫኒያ ብሄራዊ ዘብ እንዲሁም ፖሊስ በአካባቢው ተሰማርቷል። ሰኞ ምሽት በነበረው ተቃውሞም 30 የፖሊስ አባላት መጎዳታቸውን ባለስልጣናቱ አሳውቀዋል።
አንዳንድ የንግድ ተቋማትምም ግጭትን በመፍራት መስኮቶቻቸው ላይ መከላከያዎች ደራርበው ነበር ተብሏል።
የ27 አመቱ ዋላስ ባይፖላር ዲስኦርደር የሚባል የአዕምሮ ጤና መታወክ እንዳለበትም ለፖሊሶቹ ባለቤቱ ቀድማ ብትናገርም በጥይት ተኩሰው እንደገደሉት ቤተሰቡን ወክሎ ጠበቃው ተናግሯል።
በፊላደልፊያ ኮብስ ክሪክ በሚባል አካባቢ መሳሪያ የያዘ ሰው ሪፖርት በመደረጉ ሁለት ፖሊሶች አካባቢው መድረሳቸው ተገልጿል።
ዋላስ በእጁ ይዞ የነበረውን ቢላ እንዲጥል ቢጠይቁትም ዝም ብሎ ስለቀረባቸው በተደጋጋሚ እንደተኮሱበት ተነግሯል።
አንደኛው ፖሊስ ወደ ሆስፒታል ቢወስደውም ህይወቱ ልትተርፍ አልቻለችም። ፖሊሶቹ እያንዳንዳቸው ሰባት ጊዜ ተኩሰዋል ተብሏል።
የዋላስ አባት በበኩላቸው የአዕምሮ ህመምተኛ እንደሆነና መድኃኒት እንደሚወስድም ገልፀው ለምን ሌላ መንገድ አልተጠቀሙም ብለዋል።
ዋላስ ለራፕ ሙዚቃ ጥልቅ ፍቅር የነበረውና ራፐርም ነበር። በሰራቸው ሙዚቃዎች ውስጥ ስለ ጦር መሳሪያዎች፣ ፖሊስ ጭካኔ፣ የዘር ኢ-ፍትሃዊነትንም ይጠቅስ እንደነበር ዘመዶቹና ጎረቤቶቹ የተናገሩ ሲሆን ቤተሰቡንም በጣም ይወድ ነበር ብለውታል።
በሚኒሶታ በነጭ ፖሊስ አንገቱ ከመሬት ላይ ተጣብቆ በተገደለው ጆርጅ ፍሎይድም የፖሊስን ጭካኔ የሚያወግዙ በርካታ ሰዎች በፊላደልፊያ ከፍተኛ ተቃውሞን አድርገው ነበር።