ሊቢያ፡ ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች በጄኔቫ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

የሊቢያ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ታትሟል

የሊቢያ አማጺያን ኃይሎች በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለአምስት ቀናት ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር በስምምነት በማጠናቀቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸው ተሰምቷል።

በሊቢያ መንግሥት ወታደራዊ መሪዎች እና በጀነራል ሀፍታር የሚመራው የተቀናቃኝ ቡድን መካካል የተደረሰው ይሀው ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪነት የተካሄደ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ልዑክ የሆኑት ስቴፋኒ ዊሊያምስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ''ለሊቢያ ዜጎች ተስፋ የሚሰጥ ወሳኝ ምልክት ነው'' በማለት የገለጹት ሲሆን ስምምነት ላይ በመደረሱም ደስተኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት፣ ኔቶ የሚደገፈው ጦር በ2011 ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊን ከሥልጣን ካወረደ ጊዜ ጀምሮ ሊቢያ በእርስ በእርስ ጦርነት እየተለበለበች ትገኛለች።

በነዳጅ ሃብት የበለፀገቸው ሊቢያ ወደ አውሮጳ መሻገር ለሚፈልጉ አፍሪካውያን ዋነኛ መሸጋገሪያ ሆና እያገለገለች ነው።

በሊቢያ የሚካሄደው ግጭት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መካከል መከፋፈል ፈጥሯል።

ባለፈው ወር ፈረንሳይ ቱርክ በሊቢያ ላይ የተጣለውን የመሳሪያ ማዕቀብ ትጥሳለች በሚል ቅሬታ አቅርባ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት በባህር ጥበቃ ላይ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ለጊዜው ራሷን አግልላለች።

በርግጥ አንካራ እጄ የለበትም ብትልም የቱርክ መርከብ የፈረንሳይ ጦር መርከብን በሜዲትራንያን ባህር ላይ ዒላማ በማድረግ ጥቃት መክፈቱ ከተሰማ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የተለያዩ አገራት እጃቸው እንዳለበት ይገለፃል።

ሊቢያ ሁለት መንግሥት ሥር የወደቀች ሲሆን አንዱ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያገኘው በጠቅላይ ሚንስትር ፋዬዝ አል-ሴራጅ የሚመራውና መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አብዛኛውን የአገሪቱን ከተሞች የሚቆጣጠረውና በምሥራቃዊዋ ቱብሩክና ቤንጋዚ ከተሞች መቀመጫውን ያደረገው የጦር አዛዡ ጄኔራል ኻሊፋ ሃፍታር የሚመሩት ነው።

ጄነራል ሃፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ዮርዳኖስ ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጄነራሉ ጋር አድርገዋል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በሩሲያ መንግሥት ተከፋይ የሆኑ የሌሎች አገራት ቅጥረኛ ወታደሮች ከጀነራሉ ጎን ሆነው ይዋጉ ነበር። የክሬምሊን መንግሥት ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ የለኝም ብሏል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የያለውን መንግሥት ትደግፋለች። ከመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውሰጥ ተገልላ የምትገኘው ኳታር፤ በሊቢያ ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጎን ተሰልፋለች።