ቤይሩት፡ የሊባኖሱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በድጋሜ ወደ ስልጣን ተመለሱ

ታትሟል

ባለፈው ዓመት በሊባኖስ በመንግሥት ላይ የተነሳው ከፍተኛ ተቃውሞ የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሳዓድ ሃሪሪን ከስልጣናቸው አሰናብቷል።

ሳዓድ ሀሪሪ ከስልጣናቸው ከተወገዱ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የሊባኖስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃገሪቱን የሚመራ ሌላ ጠቅላይ ሚንስትር አላገኘንም፤ ስለዚህም ሳዓድ ሃሪሪን ድጋሜ ለጠቅላይ ሚንስትርነት አጭተናል ብለዋል።

አብዛኛውን የፓርላማ ድጋፍ ካገኙ በኋላ የራሳቸውን መንግሥት እንዲያዋቅሩም ሃሪሪ ተጠይቀዋል። ተቃዋሚዎቹ ግን አገሪቱ በከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ባለችበት ወቅት ባለፈው ያደረጉት ተቃውሞ የፖለቲካ ስርዓቱ ስር ነቀል በሆነ መልኩ መቀየር እንጂ ጥገናዊ ለውጥ አያስፈልገውም እያሉ ነው።

በኮሮናቫይረስ እና በነሐሴው ወር በደረሰው ፍንዳታ ሳቢያ አገሪቱ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ተገፍታለች። በርካቶች በመንግሥት ቸልተኝነት የተከሰተ እንደሆነ በሚናገሩለት የነሐሴው ፍንዳታ፣ ሃሪሪን ተክተው ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩትን ሃሰን ዲያብን ከስልጣን እንዲለቁ አድርጓቸዋል።

እሳቸውን ይተካሉ ተብለው ታጭተው የነበሩት ሙስጠፋ አዲብ ከተቃዋሚዎች ወገን በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለምርጫው ሳይበቁ ቀርተዋል።

በሃሪሪ ዘመን የሊባኖስ ምጣኔ ኃብት መውደቅ ጀምሮ ነበር። እድገቷ ወደ ዜሮ እየተጠጋ ሲመጣ በዶላር እጥረት ምክንያት የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ዋጋ እስከማጣት ደርሶም ነበር። ሥራ አጥነት እና ድኅነት እየተስፋፉ ሲሄዱ እና መንግሥት መሰረታዊ ፍላጎቶችን እንኳ ማሟላት ባለመቻሉ ተቃውሞው በርትቶ ነበር።

ይህ ተቃውሞ ገፍቶ በመሄድ ሃሪሪን ከስልጣናቸው አውርዷቸዋል። ከዚያም ተቃውሞው በመላ አገሪቱ ተስፋፍቶ ሙሰኞችና ብልሹ አሰራርን ይከተላሉ ባሏቸው ባለስልጣናት ላይ ደርሷል። ዋነኛ ሃሳባቸውም የባለሙያዎች መንግሥት እንዲቋቋም ነበር። ነገር ግን የታቀደው አልሆነም።

ሃሪሪ ስልጣናቸውን የለቀቁትም ተቃውሞውን ለማስታገስ ነበር። እሳቸው ከስልጣን መውረዳቸውን ዲያብ ተሾመዋል።

ነገር ግን ተቃውሞው አልቆመም። ተቃውሞው ቢቀጥም በሊባኖስ ምጣኔ ኃብት ላይ የተደቀነውን አደጋ ይበልጥ አባባሰው እንጅ አልቀነሰውም።

ይባስ ብሎ ባለፈው ነሐሴ ላይ የደረሰው ቃጠሎ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት የበለጠ ጎትቶታል። ከ200 በላይ ሰዎች በሞቱበት ቃጠሎ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት አድርሶባቸዋል። ከ4.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚተመን ንብረትም አውድሟል።

ሳዓድ ሀሪሪ ስልጣናቸውን የለቀቁት እነዚህ ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ለአገሪቱ መፍትሔ ለማምጣት ጭምር ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች ከበፊቱም በባሰ ሁኔታ ተባብሰዋል። ታዲያ በእነዚህ ድርብርብ ችግሮች ታጅበው ድጋሜ ለጠቅላይ ሚንስትርነት የታጩት ሳዓድ ሀሪሪ አገሪቱን ይታደጓት ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።