ናይጄሪያ አለመረጋጋት፡ በሌጎስ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ተተኩሶባቸው ሞተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በናይጄሪያዋ ትልቋ ከተማ ሌጎስ የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ተኩስ ተከፈተባቸው።
አንድ የአይን እማኝ ለቢቢሲ ወደ 20 የሚጠጋ የሰዎች አስክሬን እና 50 የሚደርሱ በጥይት ተመትተው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ተመልክቻለሁ ሲል ተናግሯል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በርካቶች ስለመሞታቸው ታማኝ መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት ደግሞ በተፈጠረው ዙሪያ ይፋዊ ምርመራ እንደሚደረግ ያስታወቁ ሲሆን ለጊዜው ለ24 ሰዓታት የሚቆይ የሰአት እላፊ ገደብ በሌጎስና አካባቢዋ ታውጇል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ናይጄርያውያን አሁንም ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ሳርስ በሚል የሚታወቀውና ዝርፊያን ለማስወገድ የተቋቋመው ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲወገድ ነው ጥያቄያቸው።
ተቃውሞውን ተከትሎ ይህ ኃይል እንደተወገደ ቢገለጽም፤ ናይጄርያውያን ግን ውሳኔውን አላመኑበትም። የልዩ ፖሊስ ኃይሉ አባላት ወደ ሌሎች ክፍሎች መዘዋወር ሳይሆን ለጥፋታቸው ተጠያቂ መደረግ አለባቸው ይላሉ።
ተቃውሞው ከናይጄርያ አልፎ አውሮፓና ካናዳ ደርሷል። ቡድኑ ሕግ ወጥ እስር እንደሚያካሂድ፣ ሰዎችን እንደሚያሰቃይና እንደሚገድልም ተቃዋሚዎቹ ይከሳሉ።
የንግድ ማዕከል በሆነችው ሌጎስን ዋና ዋና ጎዳናዎችን በመዝጋት ተቃዋሚዎቹ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ሳምንታት ተቆጥረዋል። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ በከተማዋ ዋነኛ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ሰልፍ ወጥተዋል።
በሌጎስ ተቃዋሚ ሰልፈⶉች ላይ ተከፍቷል ስለተባለው ተኩስ የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሂላሪ ክሊንተን የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀመዱ ቡሀሪ ወታደሮች ንጹሀን ታዳጊዎችን ከመድገል እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።
ናይጄሪያዊው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ኦዲዮን ኢጋሎም ቢሆን መንግሥት ዜጎቹን እየገደለ ነው ሲል ተችቷል። ''በዚህ መንግሥት ስራ በእጅጉ አፍሪያለሁ'' ሲል በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው የተንቀሳቃሽ ምስል መልእክት አስተላልፏል።
ተቃውሞው እንዴት ተነሳ?
የሳርስ አባላት አንድ ወጣትን ገድለዋል መባሉን ተከትሎ ነበር ተቃውሞው የተቀጣጠለው።
ተቃዋሚዎች ልዩ የፖሊስ ኃይሉ እንዲወገድ ጠይቀዋል። መንግሥትም የፖሊስ ኃይሉን በትኖ ሌላ ልዩ ኃይል (ስፔሻል ዌፐንስ ኤንድ ታክቲክስ) መሥርቷል።
ሆኖም ተቃዋሚዎች ማሻሻያው በቂ አይደለም ይላሉ።
ተቃውሞው የመላው ዓለምን ትኩረት የሳበ ሲሆን፤ የትዊተር ኃላፊ ጃክ ዶርሲ ድጋፉን ገልጿል።
ናይጄርያውያኑ ታዋቂ ዘፋኞች ዊዝኪድ እና ዴቪዶም ተቃውሞውን ደግፈዋል።
ልዩ ኃይሉ በዝርፊያ፣ ሰዎችን በማንገላታት፣ በግድያም ተወንጅሏል። በሳርስ አባላት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎችም የገጠማቸውን እየገለጹ ነው።
ኦቢያንኡጁ ኢያና ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ወንድሟ ቺጂኦኬ ከስምንት ዓመት በፊት በልዩ ኃይሉ ታስሮ የት እንደደረሰ አይታወቅም።
ወንድሟ እንደተገደለ ቢነገራቸውም አስክሬኑን አላዩም። የፖሊስ ኃይሉ የኋላ ኋላ ቺጂኦኬን ማሰሩን ክዷል።
"እስካሁን ይሙት ይሩር አናውቅም" የምትለው ኦቢያንኡጁ ፍትሕ ከሚጠይቁ ተቃዋሚዎች አንዷ ናት።
"ሳርስ እንዲገታ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂ እንዲደረግም እሻለሁ። ፍትሕ እፈልጋለሁ" ብላለች።














