አፍሪካ፡ የፖሊስ ጭካኔ ተቃውሞ በቀጠለባት ናይጄርያ መከላከያ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

ዝርፊያን እንዲከላከል ተቋቁሞ የነበረው ልዩ የፖሊስ ኃይል (ሳርስ) እንዲፈርስ መንግሥት ቢስማማም፤ ተቃውሞው በተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዝርፊያን እንዲከላከል ተቋቁሞ የነበረው ልዩ የፖሊስ ኃይል (ሳርስ) እንዲፈርስ መንግሥት ቢስማማም፤ ተቃውሞው በተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነው
ታትሟል

በናይጄርያ የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወመው ሰልፍ ሳምንቱን ይዟል። የአገሪቱ መከላከያ "የመንግሥትን መመርያ የጣሱ እንቅስቃሴዎች እና ችግር ፈጣሪዎች" ላላቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ማስጠንቀቂያው የተላለፈው አቡጃ ውስጥ ሰልፈኞች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በገጀራ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።

ዝርፊያን እንዲከላከል ተቋቁሞ የነበረው ልዩ የፖሊስ ኃይል (ሳርስ) እንዲፈርስ መንግሥት ቢስማማም፤ ተቃውሞው በተለያዩ ከተሞች እንደቀጠለ ነው።

ልዩ ኃይሉ በተለይም ወጣቶችን ኢላማ አድርጎ በማሰቃየት፣ በመበዝበዝና በመግደል ተወንጅሏል።

መከላከያ ምን አለ?

የመከላከያ ቃል አቀባይ ኮ/ል ሳጊር ሙሳ "የመንግሥትን መመርያ የጣሱ እንቅስቃሴዎች እና ችግር ፈጣሪዎች እንዲታቀቡ የናይጄርያ መከላከያ ያስጠነቅቃል። አገሪቱን እና ዴሞክራሲዋን ለመከላከል ዝግጁ ነን" ብለው ፌስቡክ ላይ ጽፈዋል።

መከላከያው "ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ሲቪል ማኅበራትን እንደሚያግዝ" አክለዋል።

ተቃዋሚዎች ይህን ማስጠንቀቂያ እንደ ማስፈራሪያ ወስደውታል።

ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰው ጥቃት

ትላንት አቡጃ ውስጥ የፖሊስ ጭካኔን ይቃወሙ የነበሩ ተቃዋሚዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በገጀራ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የዐይን እማኞች እንዳሉት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ተሰብስበው ሳለ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

አንድ ተቃዋሚ ከጥቃት ሰንዛሪዎች መካከል ተይዘው ለኃላፊዎች የተሰጡ እንዳሉ ጠቁሟል።

ተመሳሳይ ጥቃት በሌጎስ ተቃዋሚዎች ላይ እንደተሰነዘረም ተገልጿል።

ፖሊስ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል

መንግሥት መከላከያ ጣልቃ እንዲገባ ከፈቀደ ካለፈ ስህተቱ ምንም እንዳልተማረ ያሳያል ሲል የቢቢሲ የሌጎስ ዘጋቢ ንዱካ ኦርጂናሞ ያስረዳል።

"አዲስ ችግርን በቀደመው መንገድ ለመፍታት መሞከር ነው። ይህ ደግሞ አይሠራም" ብሏል።

በተቃውሞው ቢያንስ ዓሥር ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፤ መከላከያ ጣልቃ ከገባ ከልዩ ኃይሉም የባሰ ጉዳት እንደሚያስከትል ይናገራል።

ተቃውሞውን የሚመራው ወጣት ትውልድ እአአ 1999 ላይ የተወደገው ወታደራዊ ሥርዓትና ጭቆናው ባይደርስበትም፤ በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አይመስልም።

ተቃውሞው እንዴት ተነሳ?

የሳርስ አባላት አንድ ወጣትን ገድለዋል መባሉን ተከትሎ ነበር ተቃውሞው የተቀጣጠለው።

ተቃዋሚዎች ልዩ የፖሊስ ኃይሉ እንዲወገድ ጠይቀዋል። መንግሥትን ኃይሉን በትኖ ሌላ ልዩ ኃይል ስፔሻል ዌፐንስ ኤንድ ታክቲክስ) መሥርቷል።

ሆኖም ተቃዋሚዎች ማሻሻያው በቂ አይደለም ይላሉ።

ተቃውሞው የመላው ዓለምን ትኩረት የሳበ ሲሆን፤ የትዊተር ኃላፊ ጃክ ዶርሲ ድጋፉን ገልጿል።

ናይጄርያውያኑ ታዋቂ ዘፋኞች ዊዝኪድ እና ዴቪዶም ተቃውሞውን ደግፈዋል።

ልዩ ኃይሉ በዝርፊያ፣ ሰዎችን በማንገላታት፣ በግድያም ተወንጅሏል። በሳርስ አባላት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰባቸው ሰዎችም የገጠማቸውን እየገለጹ ነው።

ኦቢያንኡጁ ኢያና ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ወንድሟ ቺጂኦኬ ከስምንት ዓመት በፊት በልዩ ኃይሉ ታስሮ የት እንደደረሰ አይታወቅም።

ወንድሟ እንደተገደለ ቢነገራቸውም አስክሬኑን አላዩም። የፖሊስ ኃይሉ የኋላ ኋላ ቺጂኦኬን ማሰሩን ክዷል።

"እስካሁን ይሙት ይሩር አናውቅም" የምትለው ኦቢያንኡጁ ፍትሕ ከሚጠይቁ ተቃዋሚዎች አንዷ ናት።

"ሳርስ እንዲገታ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂ እንዲደረግም እሻለሁ። ፍትሕ እፈልጋለሁ" ብላለች።