ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱሪዝም፡ ጎብኚዎች የፓርክ ሰራተኛ በድቦች ሲገደል ተመለከቱ
በቻይናዋ ሻንግሃይ ከተማ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ አንድ ሰራተኛ ጎብኚዎች ፊት በድብ ተነክሶ ህይወቱ አለፈ።
ይህንን ተከትሎ ፓርኩ የደህንንት ስራውን እንደሚያሻሽል ቃል ገብቷል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በተከሰተው አደጋ የሻንግሃይ የዱር እንስሳት ማቆያ ፓርክ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ግለሰብ በድቦች ጥቃት ደርሶበት ሕይወቱ አልፋለች።
ለጉብኝት በቦታው የነበሩት ጎብኘዒዎች ባስ ውስጥ ሆነው ሁኔታውን በጭንቀትና በፍርሀት የተከታተሉት ሲሆን ከመካከላቸው ሁኔታውን በስልካቸው ቀርጸው በማህበራዊ ሚዲያ ያጋሩም ነበሩ።
የፓርኩ አስተደር ደግሞ በተፈጠረው ነገር በእጅጉ ማዘኑን በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል።
ፓርኩ በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ''በተፈጠረው ነገር በእጅጉ አዝነናል፤ አደጋውን በጭንቀት ለመመልከት ለተገደዱትም ቱሪስቶችም ይቅርታ እንጠይቃለን'' ብሏል።
ፓርኩ አክሎም አደጋው እንዴት ሊከሰት እንደቻል ምርመራ እንደሚያደርግና ከዚህ በኋላ የደህንነት አመራር ስራዎች ላይ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ በመግለጽ ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናትም ተመኝቷል።
በአሁኑ ሰአት ፓርኩ በጊዜያዊነት የተዘጋ ሲሆን ቀድመው ቲኬት ለገዙ ጎብኚዎችም የቲኬቱ ዋጋ እንደሚመለስም ተገልጿል።
በማህበራዊ ሚዲያው ዌቦ እየተሰራጨ በሚገኘው ተንቀሳቃሽ ምስል ጎብኚዎቹ በመጮህ ድቦቹን ለማባረር ሲሞክሩ የሚታይ ሲሆን ድቦቹ ግን በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው ሰራተኛውን ገድለውታል።
ፓርኩ ለዱር እንስሳቱ እንዲመች ተብሎ በጣም ሰፊ ቦታ የሚሸፍን ሲሆን ጎብኚዎችም ቢሆኑ ወደ ቦታው የሚገቡት በማመላለሻ መኪናዎች ውስጥ ተጭነው ነው። ይህን ማድረግ ያስፈለገውም እንስሳቱ እንደልባቸው ልክ እንደ ጫካ እንዲንቀሳቀሱ በማሰብ አንደሆነ ፓርኩ ገልጿል።
በዚሁ ፓርክ የተከሰተውን አደጋ በማስመልከት በርካቶች ሀዘናቸውን የገለጹ ሲሆን በፓርኩ ስላለው የደህንነትና የጥንቃቄ እርምጃዎችም ትችታቸውን የሰነዘሩ አልጠፉም።
አንዳንዶች የዱር እንስሳቱ በብረት አጥር ውስጥ ብቻ ነው መሆን ያለባቸው፤ ይህ ቢሆን ኖሮ አደጋው አይደርስም ነበር ብለዋል። ሌሎች ደግሞ እንስሳቱ እንደልባቸው መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው፤ ፓርኩ ግን ለሰራተኞቹና ለጎብኚዎች ደህንነት ማሰብ አለበት ብለዋል።