ቻይናዊውን ሚሊዮነር የገደለው አስር አመት ተፈረደበት

ሚሊየነሩ ጋንግ ዩዋን

የፎቶው ባለመብት, Court handout/Weibo

የምስሉ መግለጫ, ሚሊየነሩ ጋንግ ዩዋን
ታትሟል

ቻይናዊውን ሚሊዮነር ገድሎ ሰውነቱን የቆራረጠው ግለሰብ በካናዳ የአስር አመት እስር ተፈርዶበታል።

ቻይናውያንን ያስደነገጠው ይህ ግድያ የተፈፀመው ከአምስት አመታት በፊት ሲሆን ሚሊዮነሩ ጋንግ ዩዋን የገዳዩ ግለሰብ ዘመድ ነው ተብሏል።

ገዳዩ ሊ ዝሃዎና ሚሊዮነሩ የተጋጩ ሲሆን መጨረሻውም ጋንግ ህይወቱን እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።

ሰኞ እለት የካናዳው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎትም ገዳዩን ግለሰብ የ10 አመትና ስድስት ወራት የእስር ቅጣት ጥሎበታል።

የፍርድ ሂደቱም የካናዳና የቻይና መገናኛ ብዙኃን ቀልብን ስቧል።

ገዳዩ በድርጊቱ እንደተፀፀተና ከግለሰቡ ባህርይም ጋር የሚቃረን ነው በማለት ዳኛ ቴረንስ ሹልትስ ተናግረዋል።

"ሊ ዝሃዎን የሚያውቁትን ሰዎች ምስክርነት በሰማንበት ወቅት በዚያን ወቅት ከፈፀመው የወንጀል ድርጊት ጋር የሚቃረን ነው። ከሰው ጋር ተጋጭቶ የማያውቅ፣ ደግ፣ ልቡ ሩህሩህና ሰው ወዳጅ መሆኑንም ተናግረዋል" ብለዋል ዳኛ ቴረንስ።

ሚሊዮነሩ ጋንግ ዩዋን በገዳይነት የተወነጀለው የሊ ዝሃዎን ባለቤት የአጎት ልጅ ነው። ነዋሪነታቸውም በካናዳ ሲሆን ቤተሰቡ በሙሉ በጋንግ ቪላ ቤት ውስጥ በአንድ ላይ ነበር።

የ42 አመቱ ጋንግ ሃብቱን ያፈራው ከፔትሮሊየምና የከሰል ማዕድን ኢንዱስትሪም እንደሆነ ይናገራል። በርካታ ጊዜያትንም አግብቶ ፈትቷል።

ግድያው በተፈፀመበት በዚያች እለትም ሚሊዮነሩ የሊ ዝሃዎን ብቸኛ ልጅ ማግባት እንደሚፈልግ ይነግረዋል።

በሁኔታው የተበሳጨው ሊ ዝሃዎንም ይህ በዘመዶች መካከል የሚፈጠር ጋብቻ ነው በማለት "አውሬ ነህ" ብሎ እንደተናገረውም ከፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በዚህም ግብግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን ሊም ተኩሶበታል።

"በዚህ ወቅትም አዕምሮዬ ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አላውቅም። ሁሉ ነገር ጭልም አለብኝ" ብሏል።

በኋላም የሟቹን ሰውነት ለ108 ክፍሎች ቆራርጦም በፕላስቲክ ውስጥ ከቶም ሊጥለው ሞክሯል። ባለቤቱና አማቹም ሁኔታውን በመረዳታቸው ለፖሊስ ጠቁመዋል ተብሏል።

ከአምስት አመታት በፊት በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር ላይ የሚገኘው ሊ ቀሪው በእስር ቤት ማሳለፍ የሚጠበቅበት ጊዜ ሁለት አመት ከአራት ወር ነው።

የሚሊዮነሩ ጋንግ ሃብት 21 ሚሊዮን ዶላር የተገመተ ሲሆን ልአምስት ልጆቹም እንደሚከፋፈል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል።