ቻይናዊቷ በቀጥታ ስርጭት ላይ በእሳት ተቃጥላ ሞተች

ቲክቶክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ቻይናዊቷ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ለአድናቂዎቿ በቀጥታ ስርጭት ለማድረግ እየተዘጋጀች ሳለች ባለቤቷ ነዳጅ አርከፍክፎባት በእሳት እንዳቃጠላትና ሕይወቷ እንዳለፈ የቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ላሙ በመባል የምትታወቀው ቻይናዊት የቲክቶክን ቦታ ተክቶ በሚሰራው ዱዪን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች እንዳላት ተገልጿል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኑ እንደዘገቡት ከሆነ በደረሰባት ጥቃት ላሙ 90 በመቶ የሚሆነው የሰውነት ክፍሏ በእሳት ተቃጥሏል። ጥቃቱ ከደረሰባት ሁለት ሳምንታት በኋላም ሕይወቷ አልፏል።

የላሙ ጉዳይም በቻይና በሴቶች ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች መነጋገሪያ ሆኗል።

የ30 ዓመቷ ላሙ ከቻይናዋ ሲቹዋን ክልል የተገኘች ስትሆን የገጠር ደስተኛ ሕይወትን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን በመልቀቅና በቪዲዮቿም ላይ መዋቢያዎችን ባለመጠቀሟ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ችላለች።

የጂንቹዋን ግዛት አስተዳደር ፖሊስ እንዳለው በአውሮፓውያኑ መስከረም 14 በተፈጸመባት ጥቃት በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ክትትል ሲደረግላት የነበረ ሲሆን ለተሻለ ህክምና ደግሞ ወደ ሲንቹዋን ሆስፒታል ተዘዋውራለች።

አንድ ጋዜጣ ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ የላሙ ቤተሰበቦች ተከታዮቿ ለህክምናዋ የሚረዳ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ በጠየቁት መሰረት በ24 ሰአታት ውስጥ ብቻ አንድ ሚሊየን ዩዋን ተሰባስቧል።

ይሁን እንጂ የላሙን ሕይወት መታደግ አልተቻለም።

ፖሊስ ታንግ በመባል የሚታወቀው ግለሰብ ጥቃቱ በተፈጸመ ዕለት በቁጥጥር ስር መዋሉን የገለጸ ሲሆን ጉዳዩ አሁን በምርምራ እንደሆነ አስታውቋል።

በላሙ ሞት የተበሳጩ በርካታ ቻይናውያን በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን 70 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን የላሙን ስም በመጥቀስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አንዲት የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚም ''ሴት ፖሊሶች ያስፈልጉናል፣ ሴት ዳኛዎች እና ሴት አቃቤ ሕጎች ያስፈልጉናል። በርካታ ሴቶች ወደ ፖለቲካው ሊመጡ ይገባል፤ ሴቶች ድምጻችን ሊሰማ ይገባል፤ ኃይል ሊኖረን ይገባል'' በማለት ጠንከር ያለ መልዕክቷን አስቀምጣለች።