የአየር ትራንስፖርት፡ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የአየር ትራንስፖርተ ዘርፍ ሥራዎች አሁንም አደጋ ላይ ናቸው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኮሮናቫይረስ ምክንያት በመቶ ሺዎቹ የሚቆጠሩ የአየር መጓጓዣ ሥራዎች አሁንም አደጋ ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አስታወቀ።
290 አየር መንገዶችን የሚወክለው ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የአየር ትራፊክ በ2019 ከነበረው ከ2020 ጋር ሲነጻጸር በ66 በመቶ ይቀንሳል ሲል ተንበያውን አሳውቋል።
በማኅበሩ ቅድመ ግምት መሠረት ከወረርሽኙ በኋላ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ወደቀደመ ደረጃው የሚመለሰው ከአራት ዓመታት በኋላ በ2024 ይሆናል ብሏል።
በበርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ሁለተኛ ዙር ስርጭት መከሰቱ እና መንግሥታት አሁንም የጉዞ ክልከላዎችን መጣላቸው ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን ያክል ለውጥ እንዳያስመዘግብ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
ኮሮናቫይረስ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ ባለበት ወቅት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ መጠን መጎዳቱ ይታወሳል። ግዙፍ አየር መንገዶች፣ አየር ማረፊያዎች እና አስጎብኚ ደርጅቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ መገደዳቸውን አሳውቀው ነበር።
"አየር መንገዶች ከመንግሥት ድጋፍ አለማግኘታቸው እና ደንበሮች ዝግ ሆነው መቆየታቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን እንዲያጡ ምክንያት ይሆናል" ብለዋል የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሌክሳንደር ዲ ጁኒአካ።
"መንገደኞች ያለ ስጋት እንዲጓዙ፤ መንግሥታት ደግሞ ደንበሮቻቸውን እንዲከፍቱ ለማበረታታት አየር መንገዶች ተጓዦች ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ይዘው እንዲቀርቡ ማደረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው።
ከዚህ ቀደም 3 ሺህ 500 ሠራተኞቹን የቀነሰው ቨርጅን አትላንቲክ አሁንም ተጨማሪ 1 ሺህ 150 ሰዎችን ሊቀንስ መሆኑን አስታውቋል።
አየር መንገዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሥራ ላይ የሚቆይበትን ጊዜ በ18 ወራት ለማራዘም አቅዶ ነው ተብሏል።
የዓለማችን ግዙፉ አየር መንገድ አሜሪካን ኤርላይንስ በበኩሉ ባለፈው ወር 19 ሺህ ሠራተኞቹን እንደሚቀንስ አስታውቆ ነበር። አየር መንደጉ በወረርሽኙ ሳቢያ 30 በመቶ ሠራተኞቹን እንዲቀንስ መገደዱ ተጠቅሷል።
ሌላኛው የአሜሪካ ግዙፍ አየር መንገድ ዩናይትድ ኤርላይንስ በበኩሉ 36 ሺህ ሠራተኞቹ ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቆ ነበር።
የጀርመኑ ሉፍታንዛ 22 ሺህ ሠራተኞችን ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቋል። ብሪቲሽ ኤርዌይስ ደግሞ 13 ሺህ ሠራተኞችን ቀንሷል።














