እምቦጭ፡ ተገኘ የተባለው ፀረ እምቦጭ አረም "መድኃኒት" እና የተከተለው ውዝግብ
የአንቦጭ አረም የኢትዮጵያን ትልቁን ሐይቅ ጣና ላይ ተንሰራፍቶበት የሐይቁንና በዙሪያው የሚገኙ ነዋሪዎችን ህልውና ስጋት ውስጥ ከከተተው ዓመታት ተቆጥረዋል። አረሙ ያለመፍትሔ ከዓመት ዓመት በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ ለሌሎች በአገሪቱ ለሚገኙ የውሃ አካላት ሊተርፍ እንደሚችል እየተነገረ ቆይቷል።
በየጊዜው የሰው ጉልበትን በመጠቀም ከተወሰነው ሐይቁ ክፍል ላይ አረሙን ለማስወገድ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የተለያዩ ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ለወራሪው አረም የሚሆን መፍትሄ ለማግኘት ይሆናል ያሉትን የበኩላቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በሰው ጉልበትም በቴክኖሎጂም የተደረጉት ጥረቶች ውጤት ስላላስገኙ የአረሙ መስፋፋት እየጨመረ ይገኛል።
ሰሞኑን ግን መሪጌታ በላይ አዳሙ የተባሉ ግለሰብ ለዚህ አሳሳቢ አረም መፍትሔ የሚሆን መድኃኒት እንዳገኙ ሲናገሩ ተሰምቷል። ይህ ከዕጸዋት ተዘጋጅቶ ለሰባት ዓመታት ሙከራ ሲያደርጉበት እንደቆ የሚናገሩለት መፍትሔ እምቦጭ አረምን ድራሹን የሚያጠፋ "መድኃኒት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መሪጌታ በላይ እንደሚሉት "መድኃኒቱ" እንቦጩ ላይ ከተረጨ ከ24 ሰዓታት በኋላ አረሙን እንደሚያደርቀው ይናገራሉ። ይህንን ሥራቸውንም "በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች አሳይቼ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ" ይላሉ።
"መድኃኒቱን"ላይ የተደረገው ሙከራ
መሪጌታ በላይ የቀመሙትን መድኃኒት ወደ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በመውሰድ ለባለሙያዎች አሳይተዋል። የተግባር ሙከራም እንደተደረገበት ይናገራሉ።
ይህንንም ሙከራ በቅርበት የተከታተሉት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ መምህር የሆኑት ወ/ሮ ፍትፍቴ መለሰ ናቸው። መምህርቷ የዶክትሬት [ሦስተኛ] ዲግሪያቸውን በእምቦጭ አረም ላይ እየሰሩ ይገኛሉ።
መሪጌታ በላይ ለእምቦጭ አረም ማስወገጃነት ያገለግላል ያሉትን መድኃኒት በዩንቨርሲቲው አማካይነት ሙከራ እንዲደረግበት ሲጠይቁ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወ/ሮ ፍትፍቴ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጅ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር እንደተመደቡ ተገልጸወል።
ይህንንም ተከትሎ በግለሰቡ ተዘጋጅቶ የቀረበውን መድኃኒት በእምቦጭ አረም ላይ በማድረግ ያሳየውን ለውጥ የተመለከተ ሪፖርት አዘጋጅተው ለሚመለከተው የትምህርት ተቋሙ ክፍል ማቅረባቸውን ወ/ሮ ፍትፍቴ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሙከራው በአረሙ ላይ ከመጀመሩ በፊት መድኃኒቱን ያቀረቡት መሪጌታ በላይ የተዘጋጀው መድኃኒት ሌሎች የውሃ ውስጥ እጸዋትንና ነፍሳትን የሚጎዳ ኬሚካል መሆን አለመሆኑን ለማሳት "መድኃኒቱን" እንደጠጡት መምህርቷ ተናግረዋል።
ከዚያም በኋላ ምርምር በሚደረግበት የሙከራ ኩሬ ላይ "መድኃኒቱ" ተደርጎ "በ24 ሰዓት በኋላ በስፍራው ከነበረው የእንቦጭ አረም ውስጥ ቢያንስ 70 ከመቶ የሚሆነው ደርቆ አገኘነው" ያሉት ወ/ሮ ፍትፍቴ፤ አረሙ መቶ በመቶ ስላልደረቀ ድጋሚ እንዲረጭ ተደርጎ ሙሉ በሙሉ መድረቁን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ሙከራው በዚህ ሳያበቃ በመጀመሪያ የተገኘውን ውጤት ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ መሞከራ አስፈላጊ ስለነበረ ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ጊዜ ተሞክሮ ተመሳሳይ ውጤት መታየቱን ወ/ሮ ፍትፍቴ አረጋግጠዋል።
ነገር ግን በውሃ አካላት ላይ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው መሆኑን ለማረጋገጥ መድኃኒቱ ሌላ ቦታ ላይ መሞከር ነበረበት። በመሆኑም አሳዎች ላይ ጉዳት አለማምጣቱን ለማረጋገጥ በባሕርዳር አሳ ምርምር ተቋም ውስጥ ተሞክሮ "በአሳዎቹ ላይ በተደረገ ክትትል ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም" በማለት መስክረዋል።
"በአሳዎች ላይ የተሞከረውን መድኃኒት ግማሹን በመውሰድም እራሴ ምርምር በማደርግበት ማዕከል ውስጥ ባለ እንቦጭ ላይ ስሞክረውም አረሙን አድርቆታል" በማለት ለአራተኛ ጊዜ ውጤቱን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
መድኃኒቱ ከምን እንደተቀመመ አላውቅም፤ አረሙን ግን እንዳደርቀው አረጋግጫለሁ ያሉት ወ/ሮ ፍትፍቴ "ያየሁትን አረጋግጬ ለትምህርት ክፍሌ ሪፖርት ጽፌያለሁ።"
ጥያቄ በ"መድኃኒቱ" ላይ
ይህንን ተከትሎም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክትር ለመሪጌታ በላይ አዳሙ ስለሥራቸው ውጤት የማረጋገጫ ደብዳቤ መጻፉንም ገልጸዋል።
ነገር ግን በአማራ ክልል የጣናና የሌሎች የውሃ አካላት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) ግን ይህንን የማረጋገጫ ደብዳቤ አይቀበሉትም።
"ይህ በግለሰብ ደረጃ የተሰጠ አስተያየት እንጂ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ተካተው እና ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ የተረጋገጠ ነገር አይደለም" ይላሉ።
ቀደም ሲል መሪጌታ በላይ መድኃኒቱን እንዳገኙ ወደ እርሳቸው ቢሮ እንደሄዱ የሚገልጹት አያሌው ወንዴ (ዶ/ር)፤ የተባለውን መድኃኒትም "ከአንድ ዓመት በፊት ሙከራ አድርገንበት ውጤት አላየንበትም" ብለዋል።
መሪርጌታ በላይ ይህንን በተመለከተ "ሙከራውን ብናደርግም በተቋሙ ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች የተሰጠኝ ምላሽ አንድ ጊዜ አይሰራም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይሰራል የሚል ነበር። በመሆኑም ሁኔታው ስላላስደሰተኝ ግንኙነቴ ተቋርቷል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም መሪጌታ በላይ የሚያነሱት ጉዳይ ሥራቸውን ባቀረቡበት ጊዜ የጣናና ሌሎች የውሃ አካላት ባለስልጣን መድኃኒቱ የተቀመመበትን የእጽዋት ዝርዝር ካላወቅን አንሞክረውም መባላቸውን አንስተዋል።
ይህንንም በተመለከተ አያሌው (ዶ/ር) ትክክል መሆኑን ጠቅሰው፤ እንዳሉትም መድኃኒቱ ከዕጽዋት እንደተሰራ በቃል መነገሩ ብቻ ብቁ አያደርገውም በማለት "በውሃ አካላት ላይም ሆነ በራሱ በሐይቁ ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን አይተን ማረጋገጥ ስለነበረብን ምንነቱን ጠይቀናል" ብለዋል።
በወቅቱ እርሳቸውም ዕጽዋቱን ለማሳየት ፍቃደኛ እንዳልነበሩ የገለጹት መሪጌታ በላይ፣ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ "በአሁኑ ወቅት የአዕምሯዊ መብት ባለቤትነቴን ስላረጋገጥኩ በማንኛውም ሰዓትና ቦታ ለመሞከርም ሆነ መድኃኒቱ የተቀመመበትን እጽዋት ለማሳየት ፈቃደኛ ነኝ" ብለዋል።
አያሌውም (ዶ/ር) ማንም ቢሆን መፍትሄ አለኝ የሚል ካለ ለመቀበል ተቋማቸው ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፤ መሪጌታ በላይም "የተለየና መፍትሔ የሚያመጣ ነገር ሰርተው ከሆነ እናስተናግዳቸዋለን" ብለዋል።
ሙከራና ውዝግብ
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም መርጌታ በላይ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ጋር ለመስራት "መድኃኒቱን" ይዘው በመሄድ በዩኒቨርስቲው የሐዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አንዳርጌ ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት መሪጌታ በላይ አዳሙ አረሙን ያስወግዳል ያሉት "መድኃኒት" እንዲሞከርላቸው ዩንቨርሲቲውን በደብዳቤ ጠይቀው፤ የሐዲስ አለማየሁ የባሕል ጥናት ተቋም የተለያዩ ሙያተኞችን በማዋቀር ሙከራውን መሪጌታ በላይ ባሉበት ማካሄዱን አስታውሰዋል።
ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዚያ 6/2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኝት አካባቢ በተመረጠ አንድ ስፍራ በሚገኝ የእንቦጭ አረም ላይ ግለሰቡ ያዘጋጁት 25 ሊትር "መድኃኒት" በመርጨት መከራ መደረጉን አቶ ግዛቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ጊዜም ሙከራው የተደረገበት ቦታ ከምንም ነገር ንክኪ ነጻ መሆን ስለነበረበት ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ስፍራውን የሚከታተል ጥበቃ ተመድቦ እንደነበና ከሙከራው በኋላ የተገኘ ውጤት ካለ ለመመልከት ወደ ቦታው ሲኬድ ግን "ምንም ለውጥ አላየንም" ሲሉ ገልጸዋል።
"መድኃኒቱ" በተሞከረበት ወቅት የነበሩት መሪጌታ በላይ ግን የተገኘውን ውጤት ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር እንዲመለከቱ ቢጋበዙም ሳይሳተፉ መቅረታቸውን አቶ ግዛቸው ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ግንኙነታቸው ሙሉ ለሙሉ አቋርተዋል ብለዋል።
መሪጌታ በላይ ግን ከዩንቨርሲቲው ሙያተኞች ጋር ወደ ሙከራው ስፍራ ማምራታቸውን ቢገልጹም በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ "የመድኃኒቱን" ሙከራ ግን እንዳላካሄዱ ገልጸዋል።
"ወደ ስፍራው ሂደናል፤ ነገር ግን የመሞከሪያ ገንዳ፣ አጥር እና ጥበቃ የተደረገለት ቦታ ባለመኖሩ መድኃኒቴን አላስሞክርም ብዬ ትቼ ተመልሻለሁ" በማለት የአቶ ግዛቸውን ማብራሪያ አስተባብለዋል። ተሞክሮ ውጤት አልተገኘበትም ስለተባለው መድኃኒትም "የራሳቸውን መድኃኒት ካልሆነ በስተቀር የእኔን አልሞከርንም" ብለዋል።
እምቦጭን የሚያጠፋ መፍትሔ ለማግኘት ምርምር በሚያደርጉበትና ደረስኩበት ያሉን ውጤትም በሚያዘጋጁበት ጊዜ "ለመድኃኒቱ የሚሆን እጽዋት በበቂ ሁኔታ በአገር ውስጥ መኖሩን የዳሰሳ ጥናት አድርጌያለሁ" በማለት በቂ ግብአት እንዳለ መሪጌታ በላይ ይናገራሉ።
ስለዚህም ባዘጋጁት "መድኃኒት" እና ባለው የእጽዋትም ግብአት የጣና ሐይቅን ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ከእንቦጭ አረም ማጽዳት ይቻላል ብለው ያምናሉ። ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሌሎች ሐይቆችን ደግሞ እጽዋቱን በማልማት "መድኃኒቱን" በመቀመም ማጽዳት ይቻላል ብለዋል።

የተመዘገበው "መድኃኒት"
ይህ ያዘጋጁት ጸረ እምቦጭ "መድኃኒት" በፈሳሽና በዱቄት መልክ የተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቅሱት መሪጌታ በላይ፤ ፈሳሹን በሊትር ከ30 እስከ 50 ብር ለመሸጥ እንዳቀዱና አንድ ሊትሩ 3 ሜትር በ3 ሜትር የሆነ በአረም የተወረረር ቦታን ሊሸፍን እንደሚችል ይገምታሉ።
"የመድኃኒቱን ሙከራ ለሰባት ዓመታት ያህል በአባይ፣ ቆቃ እና ጣና አካባቢዎች አስፈላጊውን ሂደት ጠብቄ አከናውኛለሁ" የሚሉት መሪታጌ በላይ "የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት የተሰጠኝ እኔ ያቀረብኩትን መረጃ በመቀበልና በሌላ አካል ያልተሰራ አዲስ ግኝት መሆኑን በማረጋገጥ ነው" ነው ሲሉ ሥራቸው በስማቸው መመዝገቡን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የፓተንት መርማሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጣፋ ለቢቢሲ እንደገለጹት የመሪጌታ አዳሙን የእምቦጭ አረም ማጥፊያ "መፈድኃኒትን" በአነስተኛ የፈጠራ ዘርፍ ማረጋገጫ እንደተሰጠ ገልጸው፤ ይህም "በኢትዮጵያ ደረጃ አዲስ መሆኑን እና ጥቅም ሰጪ መሆኑን የሚያረጋገጥ" ነው ብለውናል።
ከዚህ በፊት የቀረበ ተመሳሳይ የምርምር ውጤት አለመኖሩን በማረጋገጥ ለመሪጌታ በላይ ማረጋገጫውን እንደሰጡ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ይህም "የቅድመ ምርምር ማረጋገጫ ነው" ብለውታል። የተሰጠው ማረጋገጫም "መድኃኒቱ" በቀጥታ ውሃ ላይ ወይም የትም ቦታ ላይ እንዲሞከር የማያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል።
ጽህፈት ቤቱ "መድኃኒቱን" በተመለከተ ቀደም ሲል በባሕርዳርና በሌሎች ቦታዎች ላይ የተደረገውን ምርምር የያዘ ጥቅል የጽሁፍ ሰነድ እና በምርምሩ ወቅት የተከተሉትን ሂደት በመገምገም ማረጋገጫውን እንደሰጠ አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ነገር ግን "ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው ምርምሩ የእርሳቸው ንብረት መሆኑን ለማረጋገጥ እንጂ፣ አገልግሎት ላይ እንዲውል እውቅ የሚሰጥ አይደለም" ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በቀጣይነት "የመድኃኒቱን" አጠቃቀም እና የጎንዮሽ ጉዳት ሊያረጋግጡ የሚችሉት የአካባቢ ጥበቃ እና ጤና ጥበቃን የመሳሰሉት ተቋማት መሆናቸውን አስረድተዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ከቀናት በፊት "መድኃኒቱን" በሚመለከት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመሪጌታ በላይ አዳሙ ለሙከራ የተዘጋጀው የእምቦጭ አረም ማጥፊያ "መድኃኒት" ላይ የውሳኔ ሐሳብ እንዳልሰጠ አመልክቷል።
ጨምሮም "መድኃኒቱ በአነስተኛ ደረጃ አረሙን ማጥፋት ቢችልም የጎንዮሽ ጉዳቱ በሳይንስናዊ ምርመራ አልተረጋገጠም" በማለት "በመድኃኒቱ" ላይ የቤተሙከራ ሥራ ለማከናወን መሪጌታ በላይ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል አልሰጡም ሲል ገልጿል።




















