ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈንጂ አነፍናፊው አይጥ የእንስሳት የጀግንነት ሜዳሊያ አሸነፈ
ፈንጂ አነፍናፊው አይጥ የእንስሳት የጀግንነት ሜዳሊያን አሸነፈ።
ሳይንሳዊ መጠሪያው 'አፍሪካን ፖችድ ራት' ነው። እጅግ ግዙፍ የሚባል በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ የአይጥ ዝርያ ነው። ፈንጂ አነፍንፎ አንዲያገኝ ለዓመታት ያሰለጠኑት ባለሙያዎች ማጋዋ የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።
ታዲያ ይህ ግዙፍ አየጥ በተለያዩ አካባቢዎች ተቀብረው የሚገኙ ፈንጂዎችን አነፍንፎ ማግኘት በመቻሉና የበርካታ ሰዎችን ህይወት በማትረፉ በእንስሳት የጀግንነት ማማ ላይ ተቀምጧል። ለዚህ ተግባሩም የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችሏል።
ማጋዋ እስካሁን ድረስ 39 የተቀበሩ ፈንጂዎችን ያገኘ ሲሆን ተጨማሪ 28 ተቀጣጣይ የጦር መሳሪያዎችን አነፍንፎ ተቁሟል።
በዩናይትድ ኪንግደም የእንስሳት በጎ አድራጎት ድርጅት 'ፒዲኤስኤ' ለማጋዋ የጀግንነት የወርቅ ሜዳሊያውን ሲያጠልቅለት ሕይወትህን በሙሉ የሰዎችን ሕይወት በማዳን ስላሳለፍክ ክብር ይገባሃል ብሎታል።
በተለይ ደግሞ ካምቦዲያ ውስጥ የተቀበሩ ፈንጂዎችን አነፍንፎ ማግኘት ላይ ይህ አይጥ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በደቡባዊ እሲያ በምትገኘው ካምቦዲያ እስከ ስድስት ሚሊየን የሚደርሱ የተቀበሩ ፈንጂዎች እንዳሉ ይታመናል።
የጀግንት ሜዳሊያው እስካሁን ከተሰጣቸው 30 እንስሳት መካከል ማጋዋ የመጀመሪያው አይጥ ነው።
የሰባት ዓመቱ ማጋዋ ስልጠናውን ያገኘው ቤልጂየም ውስጥ በተመዘገበ አፖፖ በሚባል ድርጅት ሲሆን መኖሪያው ግን በምስራቅ አፍሪካ ታንዛኒያ ነው። ሌሎች በርካታ እንስሳቶችንም ድርጅቱ ተቀብሎ ያሰለጥናል።
ማጋዋ ተወልዶ ያደገው ታንዛኒያ ውስጥ ሲሆን 1.2 ኪሎግራም ይመዝናል። ቁመቱ ደግሞ 70 ሴንቲ ሜትር ነው። ምንም እንኳን የማጋዋ ክብደትና ቁመት ከሌሎች አይጦች አንጻር ሲታይ በጣም ትልቅ ቢሆንም ፈንጂ ወረዳ ላይ ካሉት እስሳት በሙሉ ግን ቀላል ክብደት ያለው እሱ ነው።
እንደውም ክብደቱ በጣም ትንሽ በመሆኑ የተቀበረ ፈንጂ ላይ ቢራመድ እንኳ ፈንጂው አይፈነዳም።
እንደ ማጋዋ አይነት አይጦች በሚወስዱት ስልጠና ላይ በፈንጂዎቹ ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል ማነፍነፍ እንዲችሉ ነው የሚደረጉት።
ማጋዋ በ20 ደቂቃ ውስጥ አንድ ትልቅ የሜዳ ቴኒስ የሚያክል ቦታን አነፍንፎ ፈንጂ መኖር አለመኖሩን መለየት የሚችል ሲሆን አንድ ሰው ይህንን ስራ ላከናውን ቢል እስከ አራት ቀናት ሊፈጅበት ይችላል።
በአሁኑ ሰአት በቀን ለግማሽ ሰአት ብቻ የሚሰረው ማጋዋ በሚያሳዝን መልኩ ወደ ጡረታ እድሜው እየተጠጋ እንደሆነ ተገልጿል።