ቻይና በ2060 ከካርበን ልቀት ነጻ እሆናለሁ አለች

ታትሟል

ቻይና በ2060 ከካርበን ልቀት ነጻ እንደምትሆን ፕሬዝደንት ሺ ዢንፒንግ ይፋ አደረጉ።

ፕሬዝደንቱ አገራቸው የካርበን ልቀት ምጠንን ዜሮ የምታስገባበት ጠንከር ያሉ ቅድመ ተከተሎች እንደሚኖሩ በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

ይህ የቻይና ውሳኔ በካርበን ልቀጥ መጠን እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ወደተሻለ ደረጃ ይወስዳል ተብሎ ታምኖበታል። ቻይና ከጠቅላላ የካርበን ልቀት የ28 በመቶ ድርሻን በመያዝ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት ዋነኛዋ አገር ናት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርበን ልቀት መጠንን ለመቀነስ የሚደረጉ ስምምነቶች አዎንታዊ ለውጥ ሳያሳዩ በመቅረታቸው ቻይና ከዚህ መሰል ውሳኔ የመድረሷ ዜና ያልተጠበቀ ነበር።

ፕሬዝደንት ዢ አገራቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ቆርጣ መነሳቷን ለተባበሩት መንግስታት አባል አገራት ካረጋገጡ በኋላ ሌሎች አገራት የቻይናን ተምሳሌት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሺ ዢንፒንግ እንዳሉት ቻይና ከ2030 በኋላ የካርበን ልቀቷ በተከታታይ መቀነስ ከጀመረ በኋላ ነው በ2060 የካርበን ልቀት መጠኑ ዜሮ የሚሆነው። ምንም እንኳ ቻይና እአአ 2018 እና 2019 ላይ የካርበን ልቀት መጠኗ መጨመርን ቢያሳይም በኮቪድ-19 ምክንያት በ2020 የካርበን ልቀቷ መቀነስን አሳይቶ ነበር።

አሁን ላይ ዳግም ቻይና የድንጋይ ከሰል አጠቃቀሟ ላይ ማሻሻያ ባለማድረጓ የካርበን ልቀት መጨመር ምልክት እየታየ ነው። የቻይናው ፕሬዝደንት ይህን የአገራቸውን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት አሜሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ግዴለሽነት እያሳየች ባለችበት ወቅት ነው።

እአአ 2015 ላይ ፕሬዝደንት ዢ እና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ፓሪስ ላይ የካርበን ልቀት መጠንን ለመቀነስ ተስማምተው እንደነበረ ይታወሳል።

ሺ ዢንፒንግ ይፋ ባደረጉት የቻይና ውሳኔ ዙሪያ አሁንም ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ቻይና የካርበን ልቀቷን ዜሮ ለማድረስ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ምንድናቸው የሚለው አልተመለሰም።