ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ የኒውዮርክ ፖሊስ ለቻይና በመሰለል ክስ ተመሰረተበት
በኒውዮርክ ከተማ የሚገኝ አንድ ፖሊስ ለቻይና ትሰልል ነበር በሚል ክስ ተመስርቶበታል።
በቲቤት የተወለደው ባይማዳጄ አንግዋንግ በኒውዮርክ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ቻይናውያንን መረጃ በማሰባሰብ እንዲሁም የቲቤት ስደተኞችንም ሁኔታ በመሰለል ለቻይና መንግሥት መረጃ ያቀብል ነበር ተብሏል።
የአሜሪካ ዜግነት ያለው ይህ ኃላፊ፣ በፖሊስ ማህበረሰብ ጉዳዮች ክፍል ይስራ የነበረ ሲሆን በትናንትናውም እለት ነው በቁጥጥር ስር የዋለው።
ጥፋተኛም ሆኖ ከተገኘ ከፍተኛ የሚባለው 55 አመት እስራት ቅጣት ይጠብቀዋል።
አቃቤ ህግ እንዳሳወቀው በአሜሪካ ጦር የተቀጠረው አንግዋንግ የሲቪል ጉዳዮች ልዩ ባለሙያም የሚል ማዕረግም ነበረው።
በቻይና ቆንሱላ ውስጥ ከሚገኙ ሁለት ባለስልጣናትም ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበረው በሚልም ተወንጅሏል።
በኒውዮርክ ውስጥ ስለሚኖሩ የቲቤት ዜጎችን መረጃ ከማቀበል በተጨማሪ የቆንሱላ አባላቱ የኒውዮርክ ፖሊስ ኃላፊዎች በሚያዘጋጇቸው ትልልቅ ዝግጅቶችም ይጋብዛቸው ነበር።
አንግዋንግ መረጃውን በቀጥታ ለሚያቀብለው ቻይናዊ ባለስልጣንም "በፖሊስ ዲፓርትመንቱ ወደ እልቅና" ቦታ መያዝ እንደሚፈልግና ቻይናንም ወደ "ልዕልና ማምጣት" እፈልጋለሁ ማለቱን ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ አትቷል።
አንግዋንግ ከዚህም በተጨማሪ በማጭበርበር፣ ሃሰተኛ መረጃ በመስጠትና ለአንዳንድ ሂደቶችም እክል በመፍጠር ተወንጅሏል።
ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስ እንደሚያስረዳውመም ከቻይና መንግሥት በተደጋጋሚ ገንዘብ እንደተላከለት ነው።
አባቱ ከቻይና ጦር በጡረታ የተገለሉ ሲሆን የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲም አባል ናቸው። እናቱም እንዲሁ የፓርቲው አባል ሲሆኑ የመንግሥት የቀድሞ ባለስልጣን መሆናቸውንም ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አባሪ መረጃ ያስረዳል።
"በፌደራል መንግሥት በቀረበበት ክስ መሰረት ባይማዳጄ አንግዋንግ ለአገሪቱ የገባውን ቃል በሙሉ ጥሷል። ለአሜሪካ፣ ለጦሩ እንዲሁም ለፖሊስ የገባውን ቃል ኪዳን አፍርሷል" በማለት የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት ኮሚሽነር ዴርሞት ኤፍ ሺያ በመግለጫቸው አትተዋል።
በርካታ የቡድሂስት አማንያን የሚኖሩባት ቲቤት ራሷን የቻለች ግዛት ስትሆንም በቻይና ቁጥጥር ስር ናት።
ቻይና ግዛቷ በራሷ ህግ ነው የምትተዳደረው ብትልም በርካታ የመብት ተሟጋቾች ቻይና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከሷታል። ፖለቲካዊና እምነታዊ ጭቆናም አለ ቢሉም የቻይና መንግሥት ግን አጣጥሎታል።