የመረጃ መረብ ፡ በጀርመን ሆስፒታል በኮምፒውተር ጠላፊዎች ምክንያት አንዲት ታካሚ ለሞት ተዳረገች

አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የጀርመን ፖሊስ አንዲት ታካሚ በመረጃ መረብ [ሳይበር] ጥቃት ሳቢያ ሆስፒታል እያለች መሞቷን ተከትሎ የግድያ ወንጀል ምርመራ ከፍቷል።

ጠላፊዎች የጀርመኑ ዶሰልዶርፍ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የኮምፒውተር ሥርዓትን በመጥለፋቸው ምክንያት አንዲት ወደ ሌላ ሆስፒታል በመዘዋወር ላይ ያለች ታካሚ ሕይወቷ አልፏል።

የኮሎኝ ዐቃቤ ሕግ በግድየለሽነት የተፈፀመ ግድያ በሚል በጠላፊዎቹ ላይ የግድያ ወንጀል ምርመራ ከፍቷል።

ወንጀሉ ከተረጋገጠ፤ በኮምፒውተር ጠላፊዎች ምክንያት የተፈፀመ የመጀመሪያው የግድያ ወንጀል ይሆናል።

ጥቃቱ በሆስፒታሉ የኮምፒውተር አውታር ላይ የተፈፀመው ባለፈው ጳጉሜ 4/2012 ዓ.ም ነበር።

ጠላፊዎቹ የሆስፒታሉን ኮምፒውተሮች ከሥራ ውጪ አድርገዋቸው እንደነበር ተነግሯል።

በዚህ ዓመት በጣም በርካታ የኮምፒውተር ጠላፊዎች የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ፈፅመዋል።

ነገር ግን በጀርመኑ ሆስፒታል ላይ የተፈፀመው እጅግ አደገኛውና ለሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ነው ተብሏል።

ጠላፊዎቹ በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉትን አውታር ለመልቀቅ ክሪፕቶከረንሲ በተሰኘው የበይነ መረብ መገበያያ ገንዘብ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

ታካሚዋ ከነበረችበት ዶሰልዶርፍ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ሌላ ሆስፒታል ሕክምና ለማግኘት እየተዘዋወረች ነበር።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ኮምፒውተር ጠላፊዎቹ ሆስፒታሉን ሳይሆን አንድ ሌላ ዩነቨርሲቲ ላይ ጥቃት ማድረስ ነበር አላማቸው ሲሉ ዘግበዋል።

ጠላፊዎቹ በእነሱ ምክንያት የአንዲት ሴት ሕይወት ሳይጠፋ እንዳልቀረ ሲረዱ የጠየቁትን ገንዘብ ሳይቀበሉ የጠለፉትን አውታር ፈተው ተሰውረዋል።

መርማሪዎች የሴትዬዋ ሞት በጠላፊዎቹ ምክንያት ተከስቶ እንደሆን እንዲያረጋግጡላቸው የኮምፒውተር ባለሙያዎችን እርዳታ ጠይቀዋል።

ሆስፒታሉም ምርመራ ሊደረግበት እንደሚችል ተነግሯል።

ባለፈው ወር ጋርሚን የተሰኘው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ድርጅት የኮምፒውተር አውታር በጠላፊዎች በመያዙ ምክንያት በርካታ ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎ ማስለቀቁ ይታወሳል።

ሕግ አስከባሪዎች፤ ድርጅቶች ለጠላፊዎች ገንዘብ መክፈል የለባቸውም ምክንያቱም ወንጀልን ያበረታታል ሲሉ ይከራከራሉ።