ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ በፖሊስ ለተገደለችው ብሬዎና ቴይለር ቤተሰብ 12 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጥ ነው
ቤቷ ሳለች በፖሊስ ለተገደለችው ጥቁር አሜሪካዊቷ ብሬዎና ቴይለር ቤተሰቦች 12 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመስጠት የልዊስቪል ግዛት ተስማማ።
ፖሊሶች በምሽት የእጽ አሰሳ ሲያደርጉ በስህተት ብሬዎና ቤት ገብተው ቢያንስ አምስት ጊዜ ከተኮሱባት በኋላ ሕይወቷ ያለፈው ከወራት በፊት ነበር።
የ26 ዓመቷ ብሬዎና በጸረ ዘረኝነት ንቅናቄዎች ወቅት ስማቸው ከሚነሳ አንዷ ናት።
የቤተሰቦቿ ጠበቃ ሎሊታ ቤከር ካሳው ፍትሕ ለማስፈንና በፖሊስ መዋቅር ለውጥ ለማምጣት አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።
ከልዊስቪል አገረ ገዢ ግሬግ ፊሸር ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠበቃዋ “ስምምነቱ ትልቅ ቢሆንም ቤተሰቡ ብሬዎናን የገደሉ ፖሊሶች እንዲታሰሩ ይፈልጋል። የሩጫችንን የመጀመሪያ ክፍል ብናጠናቅቅም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀረናል” ሲሉ ተናግረዋል።
በግዛቱ የፖሊስ አሠራር ላይ ለውጥ ለማካሄድም ከስምምነት ተደርሷል። ከዚህ በኋላ የአንድን ሰው ቤት ለመፈተሽ ፍቃድ ሲወጣ ከበላይ አስተዳደር ይሁንታ ማግኘት ግዴታ ነው።
የብሬዎና እናት ታሚካ ፓልመር ልጃቸውን የገደሉት ፖሊሶች በሕግ ተጠያቂ እንዲደረጉ አሳስበዋል። የፖሊስ መዋቅር ላይ ለውጥ ለማምጣት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የልጃቸው ስም በጉልህ እንዲሰማም ጠይቀዋል።
ለቤተሰቡ የሚሰጠው ካሳ በግዛቱ ታሪክ ከፖሊስ ስህተት ጋር በተያያዘ የተደረገ ከፍተኛው ክፍያ ነው።
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊሶች መገደሉን ተከትሎ በአሜሪካና በሌሎች አገሮችም በተነሳው ጸረ ዘረኝነት ንቅናቄ ወቅት ስማቸው ጎልተው ከወጡ አንዷ ብሬዎና ነበረች።
የተፈጠረው ምን ነበር?
ሦሰት ፖሊሶች ብሬዎና ቤት ገብተው የተኮሱባት መጋቢት 13 ነበር። በር ሳያንኳኩና ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ለመግባት የሚያስችላቸው የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥተው ነበር።
ብሬዎና እና ጓደኛዋ ኬነት ዋከር በተኙበት ነበር ተኩስ የተከፈተው። ጓደኛዋ ከፖሊሶች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረገ በኋላ ወደ አደጋ ጊዜ የስልክ መስመር 911 ደውሏል።
ኬነት ቤታቸው እየተዘረፈ መስሎት ነበር።
ወደ 25 ጊዜ የተኮሱት ፖሊሶች ተኩስ የጀመሩት አባላቸው በጥይት ተመቶ ከቆሰለ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።
የአደጋ ጊዜ ሕክምና ባለሙያዋ ብሬዎና ስምንት ጊዜ በጥይት ተመትታ ሕይወቷ አልፏል። በቤቷም ምንም አይነት እጽ አልተገኘም።
የብሬዎና ቤተሰቦች ፖሊሶችን አላስፈላጊ ኃይል በመጠቀማቸው፣ ቸልተኝነት በማሳየታቸው እና በስህተት ሰው በመግደላቸው ከስሰዋል። ፖሊሶች እየፈለጉ የነበረው ብሬዎና ወይም ጓደኛዋን ሳይሆን በሌላ ሕንፃ የሚኖር ተጠርጣሪ ነበር።
አሰሳውን ካደረጉት ፖሊሶች አንዱ በርት ሀንክሰን ሰኔ ላይ ከሥራ ተባሯል። ጆናታን ማቲንግሊ እና ማይልስ ኮስግሮቭ ደሞ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
የከተማው የፖሊስ ኃላፊ ከሌላ የፖሊሶች ተኩስ ጋር በተያያዘ ሰኔ ላይ ከሥራ ተባሯል።
ለማኅበራዊ ፍትሕ የሚታገለው ‘አንቲል ጀስቲስ’ የተባለው ተቋም “ምንም ያክል ገንዘብ የብሬዎናን ሕይወት አይመልስም” ብሏል።
“ፍትሕ ካሳ በመስጠት አይሰፍንም። በግድያው እጃቸው ያለት ታስረው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንሻለን። ፍትሕ እንፈልጋለን” ሲሉም መግለጫ አውጥተዋል።