አስራት ሚዲያ ፡ ጋዜጠኞች በዋስትና እንዲፈቱ ቢወሰንም አለመለቀቃቸውን ጠበቃቸው ገለፁ

ታትሟል

ዛሬ [ሰኞ] ጠዋት የአራዳ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቀጠሯቸው መሰረት የቀረቡት የአሥራት ሚዲያ ጋዜጠኞች እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ ተላልፎ የነበረ ቢሆንም አለመለቀቃቸው ተነገረ።

የተጠጣሪዎቹ ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በሟሟላት በጥሬ ገንዘብ 40 ሺህ ብር ለአራቱም ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ማስያዛቸው ገልፀዋል።

ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ዋስትና በመመልከት ፖሊስ እንዲፈታቸው የመፈቻ ትዕዛዝ መጻፉን ተናግረዋል።

ጠበቃው እስረኞቹ ለሚገኙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዙን ማድረሳቸውን ገልፀዋል።

ነገር ግን ፖሊስ ተጠጣሪዎቹን "ይግባኝ ጠይቄባዋለሁ፣ የይግባኙ ሁኔታ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ አልፈታም" በማለት አለመልቀቁን ተናግረዋል።

ይግባኙን በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መከፈቱን ጠበቃው ጨምረው አስታውቀዋል።

ዛሬ [ሰኞ] የአራዳ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለአምስተኛ ጊዜ የቀረቡት የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ፖሊስ "የምሰራው ሥራ አለኝ፤ ተጨማሪ 14 ቀን ያስፈልገኛል" ቢልም ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ጥያቄን ውድቅ በማድረግ ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ፈቅዶ እንደነበር ይታወሳል።

አቶ ሄኖክ እንዳሉት በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ የፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ፖሊስ በቂ ጊዜ ተሰጥቶታል፣ ከዚህ በሁዋላ ተጠርጣረዎቹ ቢወጡ የፖሊስ ምርመራ ሂደት ለይ ምንም የሚፈጥሩት ተጽዕኖ የለም በሚል መከራካቸውንና ዋስትና መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች "አመፅ ቀስቃሽ መልዕክት በጣቢያው ሲቀርብ ሠራተኞች ነበራችሁ" በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቹ ሙሉጌታ አንበርብርና በላይ ማናዬ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያው ምስጋናው ከፈለኝ ሲሆኑ ከዘጠኝ ወር በፊት የሚዲያ ተቋሙን የለቀቀው ዮናታን ሙሉጌታም ይገኝበታል።

በጋዜጠኞቹ ላይ የቀረበው ክስም ከሕዳር 12 እስከ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ "የአማራ ሕዝብ በተለየ ተበድሏል፤ መንግሥትም የአማራ ሕዝብ ሲበደል ሊከላከልለት አልቻለም ብሎ አስተላልፏል።

"ይህ ሲተላለፍ እናንተ ሠራተኞች ነበራችሁ በማለት እንደሆነና በዚህም በኦሮሚያ ክልል ደንቢዶሎና ኦዳ ቡልቱ አካባቢ አመፅ መነሳቱን፤ ንብረት መውደሙንና የሰው ሕይወት በመጥፋቱ" መጠርጠራቸውን ፖሊስ መግለጹን ይታወሳል።