ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ
የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች 'አመፅ ቀስቃሽ መልዕክት በጣቢያው ሲቀርብ ሠራተኞች ነበራችሁ' በሚል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው ባልደረቦችና የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከትናንት በስቲያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ባለፈው አርብ በአራዳ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን ከጣቢያው መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ሽፈራው ለቢቢሲ ገለፀዋል።
በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቹ ሙሉጌታ አንበርብርና በላይ ማናዬ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያው ምስጋናው ከፈለኝ ሲሆኑ ከስምንት ወር በፊት የሚዲያ ተቋሙን የለቀቀው ዮናታን ሙሉጌታም እንደሚገኝበት አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።
በጋዜጠኞቹ ላይ የቀረበው ክስም ከሕዳር 12 እስከ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ "የአማራ ሕዝብ በተለየ ተበድሏል፤ መንግሥትም የአማራ ሕዝብ ሲበደል ሊከላከልለት አልቻለም ብሎ አስተላልፏል። ይህ ሲተላለፍ እናንተ ሠራተኞች ነበራችሁ በማለት እንደሆነና በዚህም በኦሮሚያ ክልል ደንቢዶሎና ኦዳ ቡልቱ አካባቢ አመፅ መነሳቱን፤ ንብረት መውደሙንና የሰው ሕይወት በመጥፋቱ" መጠርጠራቸውን ፖሊስ ገልጿል ሲሉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።
ይህንንም ለማጣራት መርማሪዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመላክ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ አንድ ቀን ቀንሶ ከ13 ቀን በኋላ ማለትም ለነሐሴ 13/2012 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ጌታቸው ተጠርጣሪዎች ወደ እስር ቤት ሲገቡ የሙቀት ልኬት እንዳልተደረገላቸው፣ እንዲሁም ጋዜጠኛ በላይ ማናየ የአስም ህመም ስላለበት ያለበት ክፍል ንፅህናው ካልተጠበቀ ሽንት ቤት አጠገብ በመሆኑ መቸገሩን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የታሳሪዎች ቤተሰቦችም በትናንትናው ዕለት ምግብ፣ አልባሳትና መድኃኒት እንዳይገባላቸው እንደተከለከለ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ ማቅረባቸውን ገልፀውልናል።
ቢቢሲ በትናንትናው ዕለት ያናገራቸው የተቋሙ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ጋሻው፤ ጋዜጠኞቹ ከቤት ሲወሰዱ "ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ" ከሚል ውጪ የተወሰዱበትን ምክንያት ጋዜጠኞቹም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው አለማወቃቸውን አመልክተዋል።
"የፌደራል ፖሊስና ሲቪል በለበሱ ደህንነቶች" ከቤት መጥተው እንደወሰዷቸውና ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙም ከቤተሰብ ያገኙትን መረጃ ጠቅሰው ተናግረዋል።
አቶ ተፈሪ ጋዜጠኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማጣራት ሰዎች ቢሄዱም እነርሱን ማግኘት እንደማይችሉ እንደተነገራቸውና ቤተሰብ አልባሳት፣ ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ለማድረስ በሄዱበት ወቅትም እንደተከለከሉ አስረድተዋል።
አስራት ሚዲያ ከዚህ ቀደም ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በዐቃቤ ሕግና በፖሊስ ኮሚሽን በኩል ግጭት ቀስቃሽ ተብለው ከተነሱ የሚዲያ ተቋማት ጋር አብሮ መጠራቱን በሚዲያ መስማታቸውን ያስታወሱት አቶ ተፈሪ፤ ሚዲያው የድምፃዊው ሞት ከመከሰቱ ሁለት ሳምንት በፊት በፋይናንስ ችግር ምክንያት ሥራ ላይ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
በወቅቱ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት መጠየቃቸውን የሚናገሩት አቶ ተፈሪ፤ የሚዲያ ተቋሙም ሲከሰስ የደረሰው የክስ ደብዳቤ አሊያም የፍርድ ቤት ማዘዣ አለመቀበሉን አስረድተዋል።
ይህንን ለማጣራት ጥረት ቢያደርጉም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀውልናል።
አቶ ተፈሪ "እንደ ተቋም የሰራነውን ስንገመግም ግጭት ቀስቃሽ የሆነ መልዕክት በጣቢያው አልተላለፈም። ምንም ዓይነት ምክንያት በሌለበት ነው ጋዜጠኞቹ የታሰሩት" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።