አሜሪካ፡ ለዓመታት ጥቁር ነኝ ያለችው ግለሰብ ነጭ ሆና ተገኘች

ታትሟል

አሜሪካ ውስጥ በርካታ ስራዎቿን ከአፍሪካውያን ዲያስፖራዎች ጋር ያገናኘችው መምህር ጥቁር ነኝ በማለት መዋሸቷን ተናገረች።

ጄሲካ ክሩግ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ስትሆን ከካንሳስ ሲቲ የመጣች ነጭ ይሁዳዊ ዘር መሆኗን አምናለች።

''ሕይወቴን በሙሉ ጥቁር ስለመሆኔ በተናገርኩት ውሸት ላይ መስርቼ ቆይቻለው፤ በእያንዳንዱ እስትንፋሴ ዋሽቻለው'' ስትል ጽፋለች።

ሐሙስ ዕለት በታተመው ደብዳቤዋ ላይ ጄሲካ ክሩግ የሐሰት ማንንት መገንባቷን በመግለጽ '' ምንም መብት በሌላት ቦታ ላይ ተገኝቻለው'' ብላለች።

አክላም መጀመሪያ ላይ ከሰሜን አፍሪካ የመጣች ጥቁር እንደሆነች፣ በመቀጠል ደግሞ ጥቁር አሜሪካዊ እንደሆነች እንዲሁም ከካሪቢያን የመጣች ጥቁር እንደሆነች በተለያዩ አጋጣሚዎች መናገሯን ገልጻለች።

ድርጊቷንም ''የጭካኔ ትክክለኛ ማሳያ ነው'' በማለት የገለጸችው ሲሆን ''የሌሎችን ማንንት ሰርቄያለሁ፤ ጥቁር ያልሆኑ ሰዎች በጥቁሮች ላይ የሚደርሱባቸውን ጫና በመጥፎ ተጠቅሜያለሁ፤ በግል ሕይወቴ ሳይቀር እንደ ጥቁር ቀርቤያለው'' በማለት አብራርታለች።

ጄሲካ ይህንን ሁሉ ያደረግኩት "በልጅነቴ ባጋጠመኝ አሳዛኝ ክስተተት ምክንያት በተከሰተ የአእምሮ ችግር ነው" ያለች ሲሆን ለድርጊቷን ግን ይሄ እንደ ሰበብ ሊቆጠርላት እንደማይገባ ገልጻለች።

ጄሲካ ክሩግ ምንም እንኳን ጥቁር አለመሆኗን ብታምንም ለምን ይህንን መረጃ ይፋ ለማድረግ እንደፈለገች ግን የገለጸችው ነገር የለም ተብሏል። ነገር ግን ታዋቂው የመድረክ ጸሃፊ ሃሪ ዚያድ የተባለ ግለሰብ መረጃውን ይፋ ያደረገችው ውሸቷ ስለተደረሰበት ነው ብሏል።

''ጄሲካ ክሩግ እስከዛሬዋ ጠዋት ድረስ እንደ ወዳጄ የምቆጥራት ግለሰብ ነበረች። ጠዋት ላይ ስልክ ደውላልኝ በጽሁፏ ላይ የገለጸችውን ነገር በሙሉ ነግራኛለች። ተጸጽታ ወይም ጥሩ ሰው ስለሆነች አይደለም ይህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው'' በማለት በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

አንዳንድ የዜና አውታሮች ደግሞ ይዘውት በወጡት መረጃ ጄሲካ ክሩግ ለማህበራዊ አቀንቃኝነቷ እንዲረዳት በማሰብ ጄሲካ ላ ቦምባሌራ የሚል ቅጽል ስም ትጠቀም ነበር በማለት ዘግበዋል።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ለነጭ የኒውዮርክ ነዋሪዎች በቪዲዮ ባስተላለፈችው መልዕክት ጄሲካ '' በኒውዮርክ ለሚኖሩ ጥቁሮችና ቀደምት አሜሪካውያን ጊዜያችሁን መስጠት አለባችሁ'' ብላ ነበር።

ጄሲካ ክሩግ የአፍሪካ፣ ካሪቢያን እና ዲያስፖራ ታሪኮችን የምታስተምርበት የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ የጄሲካን ጽሁፍ መመልከቱንና በጉዳዩ ላይ ግን ምንም አስተያየት እንደሌው አስታውቋል።