ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ጥቁር አሜሪካዊውን በጨርቅ ጭንቅላቱን ሸፍነው ገደሉ የተባሉ ፖሊሶች ታገዱ
በአሜሪካ አንድ ጥቁር ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባለበት ወቅት መገደሉን ተከትሎ ሰባት ፖሊሶች ከስራ ታግደዋል።
የአዕምሮ ጤና እክል ያለበት ዳንኤል ፕሩድ የተባለው ጥቁር አሜሪካዊ ፖሊሶች በጨርቅ አፍነው እንደገደሉት ተገልጿል።
ፖሊሶች ጭንቅላቱን በጨርቅ የሸፈኑት ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ላይ እንዳይተፉ የሚከላከለውን "ስፒት ሁድ' ተብሎ የሚጠራውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ተብሏል።
የግለሰቡን ሞት አስመልክቶ የሮቸስተር ከንቲባ ላቭሊ ዋረን መዋቅራዊ ዘረኝነት ነው የሞቱ ምክንያት ብለዋል።
ከንቲባ ላቭሊ በትናንትናው ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት በግድያው የተጠረጠሩት ፖሊሶችን ያገዷቸው ከምክር ቤቱ በተቃራኒ እንደሆነና ጠቅላይ አቃቤ ህግም ምርመራውን በአስቸኳይ እንድታጠናቅቅም አሳስበዋል።
"የፖሊስ ዘርፉ፣ የአዕምሮ ጤና ስርአቱም ሆነ ማህበረሰቡ ዳንኤል ፕሩድ ዘንግቶታል። እኔም ቢሆን ዘንግቸዋለሁ" ብለዋል
ከንቲባዋ በተጨማሪ የከተማዋ ፖሊስ ሃላፊ ስለ ዳንኤል አሟሟት ዝርዝር እንዳላስረዷቸው ገልፀዋል።
የግለሰቡ አሟሟት ዝርዝር የታወቀው ከሰሞኑ በፖሊስ ካሜራ የተቀረፀው ቪዲዮ ለህዝብ ይፋ መሆን አለበት የሚል ጥያቄን ተከትሎ ነው።
ከንቲባዋ እንዳሉት በቪዲዮው ያዩት የግለሰቡ አሟሟት የፖሊስ ሃላፊው ካሉት ተቃራኒ ነው። የፖሊስ ሃላፊው ግለሰቡ የሞተው ከፍተኛ አደንዛዥ ዕፅ ወስዶ ነው የሚል ምክንያት ነግረዋቸው እንደነበር ከንቲባዋ አስረድተዋል።
በፖሊስ ኃላፊው ተግባር በግልም ሆነ በሙያው ከልባቸው እንዳዘኑና "ተስፋ አስቆራጭ" ነው በማለት ገልፀውታል።
የፖሊስ ኃላፊው ሲንግልታሪ በበኩላቸው ፖሊስ የግለሰቡን አሟሟት ዝርዝር መረጃ ከህዝብ ለመደበቅ ያደረገው ነገር እንደሌለ ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።
ዳንኤል ፕሩድ የሞተው መጋቢት ወር ላይ ቢሆንም ሪፖርት የተደረገው በቅርቡ ነው።
የ41 አመቱ ግለሰብ የሞተው በነጭ ፖሊስ ታንቆ ከሞተውና አለም አቀፍ የዘረኝነትና የፖሊስ ጭካኔ ተቃውሞን ካቀጣጠለው ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት በፊት ነው።
ግለሰቡም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለበት መንገድ ከጆርጅ ፍሎይድ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ፖሊሶች ከመሬት ጋር አጣብቀውት ነበር ተብሏል።
ሰባቱ ፖሊሶች ለጊዜው ከስራ ቢታገዱም ደመወዛቸው እየተከፈላቸው መሆኑንም የከተማዋ ባለስልጣናት አሳውቀዋል።
ዳንኤል ፕሩድ እንዴት ሞተ?
የአዕምሮ ህመምተኛ የሆነው ዳንኤል ፕሩድ እርቃኑን ሆኖ በጎዳና ላይ ሲሮጥ እንዲሁም ወቅቱ በረዷማ በመሆኑ ወንድሙ ዳንኤል ለፖሊስ ደወለ።
ፖሊሶች ደርሰውም በቁጥጥር ስር ካዋሉት በኋላ መሬት ላይ አጣብቀውት ቪዲዮው ያሳያል። ግለሰቡም የፖሊሶቹን ትዕዛዝ በማክበርም ምንም ሳይንቀሳቀስ መሬት ላይ ይታያል።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም መበሳጨት እንደጀመረና ገንዘብ ወይ ሽጉጥ እንዲሰጡት ይጠይቃል። የከበቡት ፖሊሶችም ሲስቁ ይሰማል።
መሬት ላይ ምራቁን እየተፋ በቪዲዮው ላይ ይታያል። ቪዲዮው ምንም ነገር ባያሳይም አንደኛው ፖሊስ ዳንኤል ኮሮናቫይረስ ይዞኛል ስላላቸው ጭንቅላቱን በጨርቅ እንደሸፈኑት አስረድቷል።
"መትፋትህን አቁም" ብሎም አንደኛው ፖሊስ ጭንቅላቱን መሬት ላይ በሁለቱም እጆቹ ተጭኖ ሲያጣብቀው የሚታይ ሲሆን ከዚያ በኋላም እንቅስቃሴ አይታይም።
ግለሰበቡ በአምቡላንስ ሆስፒታል ተወስዶ ከሳምንት በኋላ ህይወቱ አልፏል። የህክምና ውጤቱ በደረሰበት መታፈን ሞቷል ብሏል። ዳንኤል ፕሩድ የአምስት ልጆች አባት ሲሆን ከቺካጎ በባቡር የመጣውም ወንድሙን ለመጠየቅ ነበር።
'ስፒት ሁድ' ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ላይ ምራቃቸውን እንዳይተፉ ለመከላከል በጨርቅ እንዲሸፍኗቸው የሚፈቅድ መመሪያ ሲሆን በበርካቶችም ዘንድ መታፈንና ሞት ይዳርጋልም በሚል ከፍተኛ ውግዘት ሲቀርብበት ነበር።