አውስትራሊያ፡ 19 ሺህ ዶላር ዋጋ የተተመነለት ከአዞ ቆዳ የተሰራ ቦርሳ ፈቃድ ባለመኖሩ ብቻ እንዲወድም ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Australian government
የእጅ ቦርሳ ነው፤ ከአዞ ቆዳ የተሰራ፤ ዋጋው ደግሞ 19 ሺህ ዶላር ወይንም 14 ሺህ ፓውንድ፤ በአውስትራሊያ ፍራንክ ደግሞ 26 000።
የቦርሳው ባለቤት ግን ለአገር ውስጥ ገቢ ለማስገባት የሚያስችለውን ፈቃድ ማሳየት ባለመቻሏ እንዲወድም ተደርጓል።
ይህ ቅንጡ ቦርሳ ፈረንሳይ ካለ አንድ የቅንጡ እቃዎች መደብር ነው የተሸመተው። ሱቁ ሴንት ላውረንት ቡቲክ ይሰኛል።
የአውስትራሊያ ድንበር ጠባቂዎች ፐርዝ ውስጥ ቦርሳውን መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ከአዞ ቆዳ የተሰራ ምርት ወደ አውስትራሊያ ማስገባት ይቻላል። ነገር ግን አስመጪዎቹ 70 የአውስትራሊያ ፍራንክ የሚከፈልባት የፈቃድ ወረቀት መያዝ ይጠበቅባቸዋል።
የአውስትራሊያ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ክስተቱን "ዋጋ የተከፈለበት ትውስታ ነው" በማለት ተገቢውን ሰነድ መያዝ ከኪሳራ እንደሚታደግ ተናግረዋል።
የግብርና ቢሮ፣ የውሃና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ባለሙያዎች 14 ሺህ ፓውንድ የወጣበትን ቦርሳ በቁራጭ ወረቀት ፈቃድ አለመኖር ምክንያት የተነሳ የአገሪቱን ድንበር አልፎ እንዳይገባ አድርገዋል።
በአውስትራሊያ የዱር እንስሳትን በመነገድ ወንጀል የሚያዝ አንድ ሰው የሚደርስበት ከፍተኛው ቅጣት 10 ዓመት እስር አልያም 222 ሺህ የአውስእራሊያ ፍራንክ መቀጮ ነው።
ከአዞ ቆዳ የተሰሩ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
" ሁላችንም በኦንላየን (በበይነ መረብ) ገደብ የተጣለባቸውን እንስሳት ውጤቶች ስንገዛ፣ ለመጥፋት የተቃረቡ እንስሳትን በማሰብ መጠንቀቅ አለብን" ያሉት የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሯ ሱዛን ሌይ ናቸው።
አክለውም " ህገወጥ የዱር እንስሳት ንግድን ለመቆጣጠር ወደ አውስትራሊያ የሚገቡም ሆኑ ከአውስትራሊያ የሚወጡ ነገሮችን ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል" ብለዋል።
የእጅ ቦርሳውን ከፈረንሳይ የገዛው ግለሰብ በፈረንሳይ ውስጥ የሚጠበቅበትን የግዢ ሰነድ እንዲሁም መላኪያ ያሟላ ቢሆንም፣ ወደ አውስትራሊያ ለማስገባት የሚያስፈልገውን አንድም ሰነድ ግን አላዘጋጀም ተብሏል።
በዓለም ላይ የተለያዩ መንግሥታት እንደ አዞ ያሉ እና በከፍተኛ ሁኔታ በፋሽን ኢንደስትሪው ጥቅም ላይ የሚውሉ እንስሳትን ለመታደግ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።
የአውስትራሊያ መንግሥት በህገወጥ መልኩ ወደ ግዛቱ የሚገቡ የተለያዩ እንስሳት ምርቶችን ለመቆጣጠር ጥብቅ ክትተል እንደሚያደርግ ልጿል።














