ፈረንሳይ፡ እንደራሴውን 'ባሪያ' አድርጎ የሳለው ጋዜጣ ትችት ገጥሞታል

የፎቶው ባለመብት, AFP
አንድ ቀኝ ዘመም የፈረንሳይ ጋዜጣ የሕዝብ እንደራሴዋን 'ባሪያ' አድርጎ በመሳሉ ከወዲህም ከወዲያም ነቀፋ እያስተናገደ ነው።
ቫለር አክችዌል የተሰኘው ጋዜጣ ሶሻሊስት የሆኑትን የፈረንሳይ እንደራሴ ዳኒዬሌ ኦቦኖ ልክ እንደ ባሪያ አንገታቸው ላይ የብረት ሰንሰለት የታሰረባቸው በማስመሰል ነው ያተመው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዦ ካስቴክስ 'በጣም ቀፋፊ እትም' ሲሉ የጋዜጣውን ሥራ ኮንነዋል።
ጋዜጣው እትሙ ላይ ለለጠፈው ስዕል ይቅርታ ቢጠይቅም በይዘቱ እንደማይደራደር አስታውቋል።
ጋቦን የተወለዱት እንደራሴ ኦቦኖ የፈረንሳይ ግራ ዘመም ፓርቲ ፍራንስ አንባውድ ብሔራዊ ጉባዔ ምክትል ኃላፊ ሲሆኑ ፓሪስን ወክለው ነው በሕዝብ እንደራሴነት የሚያገለግሉት።
እንደራሴዋ "ቀኝ ዘመሞች - እኩይ፣ የዘቀጠና ጨካኝ ተግባር" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።
"ይህ ምስል ለኔም ሆነ ለአያት ቅድመ አያቶቼ፤ ለቤተሰቤና ለማራምደው ፖለቲካ ስድብ ነው" ያሉት እንደራሴዋ "ከመቼውም ጊዜ በላይ ዘረኝነትን ለመዋጋት ቆርጨ ተነስቻለሁ" ሲሉ አክለዋል።
ኦቦኖ፤ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ታዋቂውን የፈረንሳይ አብዮት መፈክር ተጠቅመው "ለነፃነት፣ ለእኩልነትና ለአብሮነት" መታገላቸውን እንደማያቆሙ አስታውቀዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝደንታዊ ፅ/ቤት ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን ለእንደራሴዋ ደውለው "ለየትኛውም ዓይነት ዘረኝነት ቦታ የለኝም" ሲሉ ነግረዋቸዋል ብሏል።
የቀኝ ዘመሙ ፓርቲ፤ ናሽናል ራሊ ነባር አባል የሆኑት ዋሌራንድ ደ ሴይንት-ጀስት፤ እትሙ ለአንደራሴዋ ምንም ዓይነት ክብር አላሳየም በማለት የጋዜጣውን ድርጊት ኮንነዋል።
አሜሪካ ውስጥ ጥቁሩ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ የተቀጣጠለው የፀረ-ዘረኝነት ዘመቻ ፈረንሳይ ደርሶ ባለፈው ሰኔና ሐምሌ በርካታ ተቃውሞዎች ሲደረጉ እንደነበር ይታወሳል።
ተቃዋሚዎች የቅኝ ግዛት ዘመን የዘረኝነት ትርክት አሁንም ይስተዋላል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ፕሬዝደንት ማክሮን ፈረንሳይ ውስጥ ያለውን ዘረኝነት ለማስወገድ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ ቢናገሩም ሃገራቸው የቅኝ ገዥዎችን ኃውልት እንደማታፈርስ አስረግጠዋል።
ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የበርካታ ሰዎች ኃውልት መፍረሱና የሌሎችም እንዲፈርስ ጥያቄ መቅረቡ አይዘነጋም።
ጋዜጣው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ይፈፀመው ከነበረው ባርነት ጋር በተያያዘ ለሠራው ዘገባ ነው የእንደራሴዋን ፎቶ የተጠቀመው።












