ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማንነቱ የማይታወቀው ባንክሲ የስደተኞች መርከብን በሥዕል አስዋበ
ማንነቱ የማይታወቀው ሠዓሊ ባንክሲ፤ ስደተኞችን ሜድትራኒያን ባህርን የሚያሻግር መርከብ ላይ ሥዕል አኑሯል።
መርከቡ አደጋ ውስጥ የወደቁ ስደተኞችን የሚታደግ ሲሆን፤ ሉዊ ሚሼል የሚል መጠሪያ አለው።
ብዙዎችን ያጓጓዘው መርከቡ ባለፈው ማክሰኞ 89 ሰዎችን ይዞ እየተጓዘ ነበር።
ባንክሲ መርከቡ ላይ የሣለው አንዲት የልብ ቅርጽ ያለው የደህንነት መጠበቂያ ያጠለቀች ታዳጊን ነው።
መርከቡ ላይ ባለፈው ሳምንት የሣለው በነጭና ሮዝ ቀለም ነው።
መርከቡ መጠሪያውን ያገኘው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው ሉዊ ሚሼል ነው። መርከቡ አሁን ላይ በሙያተኞች እንደሚነዳና እነዚህ ሙያተኞች መካከል አንዳችም የሥልጣን ተዋረድ እንደሌለ ይነገራል።
የመርከቡ አላማው የሚባለው "የባህር ላይ ሕግን ማክበርና ያለ መድልዎ እርዳታ ለሚሹ ሁሉ መስጠት" ነው።
ድረ ገጹ ላይም "እኛ የሉዊ ሚሼል አባላት ሁላችንም የሰው ልጆች እንደሆንን እናምናለን። የት አገር ተወለድን የሚለው ምንም ልዩነት አያመጣም። ሰዎች ምን መብት አላቸው? እንዴትስ እንመለከታቸዋልን? የሚለው በአገር መከፋፈል የለበትም” የሚል መግለጫ ይነበባል።
በአደጋ ውስጥ ያሉ ሰዎች የእርዳታ ጥሪ ሲያቀርቡላቸው ምላሽ ይሰጣሉ።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት፤ ዘንድሮ ብቻ ከሰሜናዊ አፍሪካ ተነስተው የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ሕይወታቸው ያለፈ ወይም የጠፉ ሰዎች ቁጥር 443 ደርሷል።
ዘንድሮ ወደ አውሮፓ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 40,000 ነው።
የሠዓሊው ባንክሲ ወኪል ስለ ሥራው አስተያየት እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቦለታል።