አሜሪካ ፡ ኤፍቢአይ በጥብቅ ሲፈልገው የነበረው ተጠርጣሪ ያሲር ሰኢድ ከዓመታት በኋላ ተያዘ

ታትሟል

የአሜሪካው ወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ለ12 ዓመታት በጥብቅ ሲፈልገው የነበረው የታክሲ ሹፌር በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ያሲር አብድል ሰኢድ የገዛ ሴት ልጆቹን ገድሏል ተብሎ ነበር በፖሊስ ሲፈለግ የነበረው። በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማዘዣ የወጣበት በፈረንጆቹ 2008 ነበር።

በወቅቱ የ17 ዓመቷን ሳራህ ያሲር እንዲሁም የ18 ዓመቷን አሚና ያሲርን በመግደል ነበር የተጠረጠረው።

ትውልደ ግብፃዊው ያሲር በአሜሪካ ፌዴራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ በጣም ተፈላጊ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የገባው በፈረንጆቹ 2014 ነበር።

የ63 ዓመቱ ያሲር ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ጀስቲን የተባለ ሥፍራ ከሌሎች ሁለት ዘመዶቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ውሏል። ግለሰቡ ዳላስ ወደ ሚገኘው የኤፍቢአይ ቅርንጫፍ እንደሚወሰድ ቢሮው አስታውቋል።

የቢሮው የዳላስ ልዩ መርማሪ ማቲው ዴሳርኖ የኤፍቢአይ ሰዎች ተፈላጊውን ለዓመታት ሳይታክቱ ሲያፈላልጉት እንደነበር ተናግረዋል። የወጣቶቹ ሴቶች ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም ሲሉም ተደምጠዋል።

የልጆቹ እናት ፓትሪሺያ ኦዌንስ ግለሰቡ መያዙ ሃሴት እንደሰጣት ተናግራ 'አሁን ልጆቼ ነብሳቸው በሰላም ያርፋል' ብላለች።

ኤፍቢአይ ከያሲር ጋር ሌሎች ተጨማሪ ሰዎች መያዛቸውን ይፋ አድርጓል። አንደኛው የያሲር ወንድ ልጅ ኢስላም ሰኢድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የተጠርጣሪው ወንድም ያሲም ሰኢድ ነው።

ሁለቱ ሰዎች በወንጀል የተጠረጠረን ሰው በማስጠለል ይከሰሳሉ ተብሏል።

ያሲር የተከሰሰው በምንድነው?

የያሲር ምርመራ የተከፈተው በፈረንጆቹ ጥር 1/2008 ነበር። ይህ የሆነው ሁለት ሴት ልጆቹ በጥይት ተመተው ሞተው ከተገኙ በኋላ ነው።

በወቅቱ የታክሲ ሾፌር የነበረው ያሲር፤ ሴት ልጆቹ አሚናና ሳራህን ምግብ ቤት እንሂድ በማለት በታክሲው ይዟቸው ወጥቷል ይላል የኤፍቢአይ መዝገብ።

ከዚያም ሁለት ሴት ልጆቹን ኧርቪንግ ወደተባለ ቦታ ወስዷቸው ታክሲ ውስጥ እያሉ በመሣሪያ በተደጋጋሚ ተኩሶ ገድሏቸዋል ሲል የወንጀል ምርመራ ቢሮው ተፈፀመ ያለውን ያስረዳል።

ልጆቹን ከመግደሉ በፊት በተለይ ሳራህ የተባለች ልጁ ሙስሊም ካልሆነ ወንድ ጋር ግንኙነት በመጀመሯ እንደሚቀጣት ሲዝት ነበር ሲሉ የቤተሰቡ አባላት ለኤፍቢአይ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የኧርቪንግ ከተማ ፖሊስ ሁለት ሴቶች ሞተው ካገኛቸው በኋላ ጥር 2/2008 አባታቸው ያሲር በቁጥጥር ሥር እንዲውል ማዘዣ አውጥቶ ነበር።

ነገር ግን ያሲር ሊገኝ አልቻለም።

ሰውዬውን ለዓመታት የፈለጉት የኤፍቢአይ መርማሪዎች በስተመጨረሻም ከ12 ዓመታት በኋላ ረቡዕ ነሃሴ 26/2020 በቁጥጥር ሥር ሊያውሉት ችለዋል።

"ሰውየውን መያዛችን በስተመጨረሻም ፍትህ ለሳራህና ለአሚና ልናደርስ መሆኑ ማሳያ ነው" ይላሉ ልዩ መርማሪው ዴሳርኖ።

የሟቾቹ ቤተሰቦች በሰውዬው መያዝ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።