ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ፡ 53 ሰዎች ብቻ ያሉት ጎሳ ኮሮናቫይረስ አስግቶታል
ሕንድ ውስጥ ባሉ ትናንሽ ደሴቶች ላይ የሚኖሩት አንዳማን የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ስጋት ሆኖባቸዋል።
አራት የታላቁ አንዳማን ጎሳ አባላት ኮቨድ-19 ተገኝቶባቸዋል። ሁለቱ ወደ ሆስፒታል ገብተዋል። የተቀሩት ሁለቱ ደግሞ ለይቶ ማቆያ ናቸው።
የታላቁ አንዳማን ጎሳ አባላት 53 ናቸው። ሕንድ ውስጥ ባሉ 37 ትናንሽ ደሴቶች ላይ ነው የሚኖሩት።
ምስራቃዊ አንዳማንና ኒኮባር ውስጥ ባሉ ደሴቶች ላይ ከሞነሩ ሰዎች መካከል 2985 ሰዎች እስካሁን በበሽታው መያዛቸው ይፋ ሆኗል። 41 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሞተዋል።
እየጠፉ ያሉት የታላቁ አንዳማን ጎሳ አባላት የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ታማሚ የመዘገቡት ባለፈው ሳምንት ነው።
53ቱም የጎሳው አባላት ምርመራ እንደተደረገላቸው ለቢቢሲ የተናገሩት የጤና ባለሙያው ዶክተር አቪጂት ሮይ ናቸው።
የሕንድ የአስቸኳይ ጊዜ የጤና ባለሙያዎች ለቀናት በመኪናና በጀልባ ተጉዞው ነው ወደ ደሴቶቹ የደረሱት። ምርመራውን ያጠናቀቁት በአንድ ቀን ነው።
"ሁሉም ተባባሪዎች ነበሩ" ይላሉ ዶ/ር ሮይ።
ዶክተሩ እንደሚሉት አብዛኛዎቹ የጎሳው አባላት ብሌር ወደተባለ ወደብ በየቀኑ ጉዞ ያደርጋሉ፤ ቫይረሱን ያገኙትም በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።
ቫይረሱ እየተመናመኑ ወዳሉ ጎሳዎች ዘልቆ ገብቶ ጥፋት እንዳያደርስ እየተረባረቡ እንዳለ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
'ለዚህም ነው አንዳንድ ጎሳዎችን ሙሉ በመሉ መመርመር የያዝነው።'
አንዳማን አምስት ቁጥራቸው እየተመናመነ ያለ ጎሳዎች መገኛ ሥፍራ ነው። እነዚህም ጃራዋ፣ ሰሜን ሴንቲኔል፣ ታላቁ አንዳማን፣ ኦንጌ እና ሾምፔን ናቸው።
ጃራዋና ሰሜን ሴንቲኔል የሚባሉት ጎሳዎች ከሌሎች የሕንድ ጎሳዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም።
በተለይ ሰሜን ሴንቲኔል የተሰኙት ጎሳዎች ማንም ሰው ከውጭ እንዲመጣባቸው አይፈልጉም። ወደ ደሴታቸው የሚመጣ ፀጉረ ልውጥ አደጋ ሊደርስበት ይችላል።
በፈንረጆቹ 2018 አሜሪካዊው ጆን አለን ቻው ወደ ደሴታቸው ሲቀርብ ተመልክተው ከርቀተ በቀስት ወግተው መግደላቸው አይዘነጋም።
ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የተባለ ተቋም በ1850ዎቹ ብሪታኒያ ሕንድን ስትወር የታላቁ አንዳማን ሕዝብ ቁጥር ከ5 ሺህ በላይ ነበር ይላል። በወረራው ወቅት በገባው በሽታ ምክንያት ነው ቁጥራቸው የተመናመነው ይላል።
በፈረንጆቹ 2010 ታላቁ ቦዋ የተባሉ ሽማግሉ የጎሳው አባል በ85 ዓመታቸው መሞታቸው ይታወሳል። አዛውንቱ የጎሳውን ቋንቋዎች የሚናገሩ የመጨረሻው ሰው ነበሩ።
በሌላ በኪል 476 አባላት ያሉት የጃራዋ ጎሳ አባላት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመስፋፋቱ በፊት ቫይረሱአ እንዳይደርስባቸው በማሰብ ራቅ ወዳለው የደሴት ጫካ መዘዋወራቸውን ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
ከ115 በላይ አባላት እንዳሉት የሚገመተው የኦንጊ ጎሳ ደግሞ አንድ ደሴት ላይ ሰፍሮ ይኖራል። የጎሳውን አባላት ለመመርመር የጤና ባለሙያዎች ተልከዋል። የሾምፔን ጎሳ አባላትም ምርመራ ይደርግላቸዋል።
10 ደሴቶች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ዶክተር ሮይ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ብራዚልና ፔሩ ውስጥ የሚኖሩ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ጎሳዎች በቫይረሱ ምክንያት ክፉኛ ተጠቅተዋል። በብራዚል አማዞን ጫካ ከሚኖሩ ቀደምት ጎሳዎች መካከል 280 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት መሞታቸው ተዘግቧል።