በአውስትራሊያ 3.5 ኪ.ግ የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ ክፋዮች ተገኙ

AUSSIEGOLDHUNTERS/DISCOVERYCHANNEL

የፎቶው ባለመብት, AUSSIEGOLDHUNTERS/DISCOVERYCHANNEL

ታትሟል

እስከ 12 ሚሊየን ብር ሊያወጡ እንደሚችሉ የተገመቱ ሁለት የወርቅ ክፋዮች ደቡባዊ አውስትራሊያ ውስጥ በቆፋሪዎች መገኘታቸው ተዘግቧል።

ብሬንት ሻኖን እና ኢታን ዌስት የተባሉት ግለሰቦች 3.5 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ ክፋይ ያገኙት በቪክቶሪያ ግዛት በምትገኘው ታርናጉላ ከተማ ወስጥ ነው።

እነዚሁ ዕድለኛ ፈላጊዎች ያገኙትን ወርቅ በተመለከተ ከትናንት በስቲያ በአገሪቱ ታዋቂ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበዋል።

ሁለቱ ሰዎች ወርቆቹን ለማግኘት አካባቢውን በጥልቀት ከቆፈሩ በኋላ ብረት ነክ ነገሮችን ከርቀት መለየት የሚችል መሳሪያ በመጠቀም ነው።

"በእውነት እነዚህ ወርቆች ሁሉንም ነገር መቀየር የሚችሉ ናቸው፤ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ትልልቅ የወርቅ ከክፋዮቹን ማግኘት ማለት በጣም አስደናቂ ነገር ነው'' ሲል ኢታን ዌስት ለሲኤንኤን አስተየቱን ሰጥቷል።

ሁለቱ ግለሶች ያገኟቸው የወርቅ ክፋዮች በአንድ ላይ ሲመዘኑ ክብደታቸው 3.5 ኪሎግራም እንደሚሆን ተነግሯል።

ግኝታቸውም ዲስከቨሪ ቻናል ላይ ለዕይታ በቅቷል።

AUSSIEGOLDHUNTERS/DISCOVERYCHANNEL

የፎቶው ባለመብት, AUSSIEGOLDHUNTERS/DISCOVERYCHANNEL

ብሬንት ሻኖን በበኩሉ ''ዕድለኛ እንደምንሆን ገምቼ ነበር፤ መሬቱም ቢሆን ምንም ያልተነካ ነበር። ይህ ማለት ደግሞ ማንም ሰው ቆፍሮት አያውቅም ማለት ነው'' በማለት ለዝግጅቱ አስተባባሪዎች ተናግሯል።

አክሎም ባለፉት አራት ዓመታት በርትቶ የወርቅ ፍለጋውን አጠናክሮ ሲሰራ የነበረ እንደሆነና በሺዎች የሚቆጠሩ አነስተኛ ቁራጮችን ሲያገኝ እንደነበረ ገልጿል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ሁለቱ ግለሰቦች ያገኟቸው የወርቅ ጉማጆች መጀመሪያ ከተገመተላቸው ዋጋ በ30% የተሻለ ወጋ ሊያገኙባቸው እንደሚችሉ ጠቁማዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 አንድ አውስትራሊያዊ ቆፋሪ በተመሳሳይ ብረት ነገሮችን ከርቀት የሚለይ መሳሪያ በመጠቀም 1.4 ኪሎግራም የሚመዝን ወርቅ ካገኘ በኋላ በ3.6 ሚሊየን ዶላር አካባቢ መሸጡ የሚታወስ ነው።