ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስደተኞች፡ በሊቢያ በደረሰ የጀልባ አደጋ 5 ሕፃናትን ጨምሮ በርካቶች መሞታቸው ተሰማ
በሊቢያ ባህር ዳርቻ ባጋጠመ የጀልባ አደጋ አምስት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ 45 ስደተኞች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።
ጀልባዋ ከ80 በላይ ሰዎችን አሳፍራ እያቀናች ሳለ ዝዋራ የተባለ የሊቢያ ባህር ዳርቻ የሞተር ፍንዳታ እንዳጋጠማት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።
ይህ አሳዛኝ መርዶ የተሰማውም በአካባቢው አሳ አስጋሪዎች እርዳታ ከተረፉት 37 ስደተኞች ነው።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ዓለም አቀፉ የስደተኛ ድርጅት ስደተኞቹ ፍለጋና የነፍስ አድን ሥራ መሻሻል እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።
ድርጅቶቹ እንዳሉት ትኩረት ተሰጥቶ ካልተፈለጉና የነፍስ አድን መንገድ ካልተፈጠረ በሜዲትራኒያን ባህር አሁንም የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሊጠፋ ይችላል ብለዋል።
በዚህ ዓመት ብቻ ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመግባት የሜዴትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ከ300 በላይ ሰዎች የባህር ሲሳይ ሆነው ቀርተዋል።
ቁጥሩም ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይታመናል።
የሊቢያ የቀድሞ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱና ከተገደሉ አነስቶ አገሪቷ የበርካታ ስደተኞች ቁልፍ መሸጋገሪያ ሆናለች።
ይሁን እንጅ በአገሪቷ ባለው ግጭት፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ያለ ማስረጃ የሚፈፀሙ እስር ሳቢያ በዚያ ያለው ሁኔታው ለስደተኞቹ እጅግ አደገኛ ነው።
ረቡዕ እለት አደጋ ካጋጠማት ጀልባ የተረፉት ስደተኞች በአብዛኛው ከሴኔጋል፣ ማሊ ፣ ቻድ እና ጋና የተሰደዱ ሲሆኑ ሊቢያ ከደረሱ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በሊቢያ ስደተኞቹ በተለይ በሰዎች አዘዋዋሪዎች ወይም ታጣቂዎች እጅ ከገቡ አሰቃቂ የሆነ ድርጊት እንደሚደርስባቸው ሪፖርቶች ያመልክታሉ።
የተለያዩ ጥቃቶች ይፈፅሙባቸዋል፤ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉም ያስገድዷቸዋል።