ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ችግር ውስጥ የገቡት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች
ድህነትና ችግር በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ የበርካታ ስደተኞች እውነታ ነው። የኮቪድ1-19 ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊ ጫና ማሳደር ከጀመረ ወዲህ ደግሞ ነገሮች እየተባባሱ መጥተዋል።
ልክ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተግባራዊ መደረግ ሲጀምሩ ስደተኞችን ጨምሮ በርካታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ለችግር ተጋልጠዋል።
በቅርብ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተጣለባቸው የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ጋር ሲነጻጸር ገደቡ እንዲነሳ ቅሬታቸውን ያስገቡ ሰዎች ቁጥር በ500 በመቶ ጨምሯል።
ይህ ቁጥር የእንቅስቃሴ ገደቡ በአገሪቱ የሚገኙ የገንዘብ ችግር ያለባቸው ቤተሰቦችን ሕይወት ምን ያክል ከባድ እንዳደረገባቸው እንደ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ስደተኞች ላይ ባደረገው ጥናት መሰረት ከአውሮፓ ሕብረት ውጪ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 1.4 ሚሊየን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ከመንግሥት ማንኛውም አይነት ድጋፍና ጥቅማጥቅም ማግኘት አይችሉም።
እነዚህ ድጋፎች የልጆች ማሳደጊያ ጥቅማጥቅም፣ የግብር ጥቅማጥቅምና የአካል ጉዳተኞች ድጎማን ያካትታሉ። ስደተኞቹ እንዚህን ድጋፎች ከመንግሥት ማግኘት ስለማይችሉ ፊታቸውን ወደ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለማዞር ተገድደዋል።
ስደተኞች ላይ የሚሰራው ምግባረ ሰናይ ድርጅት 'ጄሲደብልዩአይ' እንደሚለው በ53 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምክር አገልግሎቶች በተጨማሪ ለስደተኞች የምግብ፣ ገንዘብና አልባሳት ድጋፍ ለማድረግ ተገድዷል።
'' በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሰዎች ከዚህ በፊት ይሰሯቸው የነበሩ ተባራሪ እንኳን ስራዎች መስራት አልቻሉም'' ይላሉ ድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳትቢር ሲንግ።
'' እነዚህ ሰዎች በተለይም ስደተኞች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ነበር የሚመሩት። ስለዚህ ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ በርካቶች ወደ ጎዳና ለመውጣት ተገድደዋል፤ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል እንዲሁም ተገቢ የሆነ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም።''
ጀርማያህ (ትክክለኛ ስሙ አይደለም) ከአንዲት አፍሪካዊት አገር ወደ ዩኬ የመጣው ሕጋዊ የሆነ ስራ ለአጭር ጊዜ ሰርቶ ሰርቶ እራሱንና ቤተሰቡን ለመደገፍና ወደ አገሩ ለመመለስ በማሰብ ነበር።
ነገር ግን ላለፉት 16 ዓመታት በዩናይትድ ኪንግደም ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ለንደን ውስጥና አካባቢዋ በግንባታ ሰራተኝነት ይተዳደራል። በአሁኑ ሰአትም ከባለቤቱና ሶስት ልጆቹ ጋር በመኖር ላይ ይገኛል።
ከእንቅስቃሴ ገደቡ በኋላ ግን የቤቶች ግንባታ ስራው በመቆሙ እሱም ስራ አጥ ለመሆን ተገድዷል። ቤተሰቡን በአግባቡ መመገብና የሚፈልጉትን ነገር ማሟላትም ቢሆን ከባድ ሆኖበታል።
ምንም እንኳን ላለፉት ዓመታት ከሚሰራው የዕለት ስራ ላይ ለአገሪቱ መንግሥት እየከፈለ የቆየ ቢሆንም እንግሊዝ ውስጥ የተወለዱት ሶስቱም ልጆች ድጋፉን ማግኘት አልቻሉም።
'' ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ምንም አይነት ስራ መስራት አልቻልኩም። በዚህ ምክንያት በርካታ እንቅልፍ አልባ ምሽቶችን አሳልፌያለሁ። መላው ቤተሰቤ በቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር ምግብ የሚበላው። ልጆቼ ከነጭራሹ እንዳይራቡብኝ ነው ይህንን የማደርገው'' ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።
በአሁኑ ሰአት ጀርማያህ እና ቤተሰቡ በመንግሥት ሊያገኙት ስለሚገባው ጥቅማጥቅም ያስገቡት ማመልከቻ ተቀባይነት በማግኘቱ ካለፉት ወራት የተሻለ ህይወት እየመሩ እንደሆነ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።
ነገር ግን የጀርማያህ እና ሌሎች መሰል ቤተሰቦች ለወራት እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ሆነው ሕይወትን መግፋታቸው በርካቶችን አስቆጭቷል።
የዜጎች ምክር ሰጪ ቢሮ እንደሚለው ኮቪድ-19 ዓለማቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ ከታወጀ ወዲህ በእያንዳንዱ 20 ደቂቃ ስደተኞች የድጋፍ ጥያቄ ለመቅረብ ስልክ ይደውሉ ነበር።
ሌላኛው ስደተኞች ላይ የሚሰራው 'ካልሳ ኤድ' የተባለው ምግባረ ሰናይ ድርጅት ደግሞ መንግሥት ቃል ገብቶት የነበረውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጿል።
ድርጅቱ በእንቅስቃሴ ገደቡ ወቅት ስደተኞችና ለትምህርት የመጡ ወጣቶችን ለመርዳት ጥረት ሲያደርግ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችም አሁንም ቢሆን ተገቢውን ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ ለኮሮረናቫይረስና ለከፋ ድህነት መጋለጣቸው እንደማይቀር ድርጀቱ አሳስቧል።