ኮሮናቫይረስ፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በቫይረሱ የተያዙባት ደቡብ አፍሪካ መመሪያዎቿን አላላች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡበ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ያወጣቻቸውን መመሪያዎች ለማላላት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ባስታወቁበት እለት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጣሪያው ላይ ደርሷል ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዳሉት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ መመሪያዎቹ ይላላሉ።
በአገሪቱ አወዛጋቢ የነበረው የአልኮል መጠጦችና የሲጋራ ሽያጭ እገዳም ይነሳል።
ከዚህም በተጨማሪም የአገር ውስጥ ጉዞዎች፣ ቁጥሩ የተወሰነ የቤተሰብ ስብስብ ተፈቅዷል፤ እንዲሁም ጥቃቅን የንግድ ተቋማትም እንዲከፈቱ ተወስኗል።
ፕሬዚዳንቱ በትናንትናው ዕለት በአገሪቷ ቴሌቪዥን ቀርበውም የመመሪያዎቹ መላላት ዳሽቆ የነበረውን የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ያንሰራራዋል በማለት ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም ደቡብ አፍሪካውያን እንዳይዘናጉ አሳሳስበዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የተስፋ ፍንጣቂ ቢታይም በጥንቃቄ ካልታለፈ መጪው ጊዜ ሊጨልም እንደሚችል ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ቀዳሚ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ 570 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፤ 11 ሺህ 500 ዜጎቿንም አጥታለች።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቷ ብቻ ሳይሆን በአለምም አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሩሲያና ህንድ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር የአለማችን አራቱ ቀዳሚ አገራት ሆነዋል።
ሆኖም በደቡብ አፍሪካ በቀን ውስጥ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑም ተገልጿል። በባለፈው ሳምንትም የተገኘው መረጃ እንደጠቆመው ከ12 ሺህ ወደ 5 ሺህ መቀነሱን ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከህሙማኑ መካከል 80 በመቶዎቹ ማገገማቸውንና በህክምና ላይ ያሉት ዜጎችም ቁጥር ወደ 105 ሺህ ማሽቆልቆሉን ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።
"የባለፉትን አምስት ወራት ስንገመግም ደቡብ አፍሪካ ጣሪያው ላይ እንደደረሰች ተረድተናል፤ ከዚህ በኋላ እያሽቆለቆለ ነው የሚሄደው" በማለት ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።
ደቡብ አፍሪካ ወረርሸኙን እንዴት ተቆጣጠረችው?
በኮሮናቫይረስ የተጠቃ ሰው ከተገኘባት እለት ጀምሮ ደቡብ አፍሪካ ጥብቅ የሚባሉ መመሪያዎችን አስተላልፋለች።
ከመጋቢት ወር ጀምሮም ድንበሮቿን፣ ትምህርት ቤቶችና የንግድ ተቋማትን ዘግታለች፤ የአልኮል መጠጦች ሽያጭ ታግዷል፤ ዜጎችም በቤታቸው ብቻ እንዲወሰኑ አድርጋለች።
እነዚህ መመሪያዎች የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭትን በፍጥነት እንዳይስፋፋ ያገቱት ሲሆን ይህም የጤናው ዘርፍ ለህሙማኑ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እንዲያቀርቡ አስችሎታል።
ሆኖም የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት አሽመድምዶታል ተብሏል። የአገሪቱን የምጣኔ ኃብትም ለመታደግ መንግሥት አንዳንድ የንግድ ተቋማትን በሰኔ ወር እንዲከፈቱ ቢወስንም በሐምሌ ወር እነዚህ ውሳኔዎች እንዲቀለበሱ ተደርጓል።
አገሪቷም በትናንትናው ዕለት ያነሳችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አስተላልፋ ነበር።
በደቡብ አፍሪካም ክፉኛ የተጠቃችው የንግድ ማዕከል የሆነቸው የጉዋተንግ ግዛት ናት። በወረርሽኙ ምክንያትም የአገሪቱ ጤና ማዕከላት እንደተዳከሙም ተገልጿል።














