ሃሪኬን ኢሳያስ ቢያንስ አራት ሰዎችን ገደለ

ሃሪኬን ኢሳያስ ቢያንስ አራት ሰዎችን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሃሪኬን ኢሳያስ የአትላንቲክ የባህር ዳርቻ አካባቢ ያሉ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞችን መትተወል።

ሁለት ሰዎች ደንገተኛ የንፋስ ሽክርክሪት ምክንያት መሞታቸው ተዘግቧል። ኒው ዮርክና ሜሪላንድ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች በሃሪኬን ኢሳያስ ምክንያት መሞታቸው ታወቋል።

ብሔራዊው የሃሪኬን ማዕከል ይህ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል አስታውቋል።

በሰዓት 100 ኪሎሜትር የሚጓዘው አውሎ ነፋስ በኒው ዮርክ ግዛት ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል ተፈርቷል።

ከሰሜን ካሮላይና እስከ ኒው ዮርክ ብቻ 3.4 ሚሊዮን ሰዎች ሃሪኬን ኢሳያስ የኤሌክትሪክ መስሶዎችን በመገነዳደሱ ምክንያት ጨለማ ውስጥ ናቸው።

ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ ኢሳያስ በሰዓት 65 ኪ.ሜትር ፍጥነት ወደ ሰሜን አሜሪካ እየተጓዘ ነው። ፍጥነቱንና ኃይሉን አጠናክሮ ወደ ደቡባዊ ካናዳ እየገሰገሰም ነው ተብሏል።

የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ዴ ብላዚዮ የተወሰኑ የከተማዋ አካባቢዎች አውሎ ነፋሱ ቀለል ሲል ወደ እንቅስቃሴ ይመለሳሉ ብለዋል።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ በአውሎ ነፋሱ ምክንያት አንድ ዛፍ ወድቆ መኪና ውስጥ የነበረ ግለሰብ ገድሏል፤ ሌላም አንዲት ሴት በተመሳሳይ መኪና ውስጥ ሳለች ዛፍ ወድቆባት ሞታለች ብሏል።

የኒው ጀርሲ ገዢ ፊል መርፊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡም አሳስበዋል።

የኒው ዮርክ ግዛት ባለሥልጣናት ደግሞ ለአደጋ ጊዜ የሚሆኑ እንደ የታሸገ ውሃ እና መሰል አቅርቦቶችን እያደሉ ነው።

ሃገረ ገዥ አንድሪው ኩሞ የኒው ዮርክ ግዛት ነዋሪዎች በተቻለ መጠን ከቤታቸው እንዳይወጡ አደራ ብለዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን ካሮላይና ግዛትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ሮይ ኩፐር ኢሳያስ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ሁሉም ቅዳመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

ሃሪኬን ኢሳያስ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት መምጣቱ ሁኔታውን ለአሜሪካ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባታል።

ኢሳያስ ያዳርሳቸዋል የተባሉ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎች በተቻለ መጠን በዚህም ጊዜ ቢሆን ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እያሳሰቡ ነው።