'ሃሪኬን ኢሳያስ' የተባለው ንፋስ የቀላቀለው ዝናብ የበርካቶች ስጋት ሆነ

ታትሟል

በሰዓት 140 ኪሎሜትር የሚጓዘውና 'ሃሪኬን ኢሳያስ' የተባለው ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ የአሜሪካዋን ሰሜን ካሮላይን ግዛትን እና የባህር ዳርቻዎችን ክፉኛ መምታቱ ተገለፀ።

'ኢሳያስ' በደቡብ ካሮላይና ግዛት ድንበር የደረሰው ማክሰኞ ዕለት ምሽት አምስት ሰዓት ላይ የነበረ ሲሆን፤ ከፍተኛ ጎርፍ አስከትሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችም የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል።

ብሔራዊ የሃሪኬን ማዕከልም በጣም አደገኛ የሆነና ለሕይወት የሚያሰጋ ጎርፍ እንደሚከሰት ከወዲሁ አስጠንቅቋል።

ንፋስ የቀላቀለው ይህ አውሎ ንፋስ ወደ ቨርጂኒያ፣ ኒው ጀርሲ እና ኒው ዮርክ እያመራ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢሳያስ በዚህ ዓመት ላጋጠመ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ የተሰጠ ዘጠነኛ ስም ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የካረቢያን ደሴቶችን ከመታ በኋላ በትሮፒካል የሚያጋጥም ክስተት ነው በሚል ቀለል ተደርጎ ተወስዶ ነበር። ይሁን እንጂ ሰኞ እለት ወደ ካሮላይና በመድረሱ ምድቡ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

አሁን ላይ ወደ ምስራቃዊ ባህር ዳርቻዎች በፍጥነት እያመራ እንደሆነ የብሔራዊ ሄሪኬን ማዕከል አስታውቋል።

የሰሜን ካሮላይና አስተዳዳሪ ሮይ ኮበር አርብ ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ አሳስበዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም ነዋሪዎች ራሳቸውን ከዚህ አደጋና ከቫይረሱ እንዲጠብቁ አሳስበው፤ መንግሥት ሰዎች አካላዊ እርቀታቸውን ጠብቀው የሚቆዩባቸው መጠለያዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢሳያስ የተባለው ይህ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ፍሎሪዳን አናውጦ ያለፈ ሲሆን በዶሚኒካን ሪፐብሊክ እና ፖርቶሪኮ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ገድሏል።

ከዚህም ባሻገር ዛፎችን ከስራቸው ገንድሷል፣ አዝዕርትና ቤቶችን አውድሟል፤ ጎርፍና የመሬት መንሸራተትም አስከትሏል።