ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከግድያ ሙከራ የተረፉት ፖለቲከኛ ለፕሬዝደንትነት ታጩ
ታዋቂው ታንዛኒያዊው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ቱንዱ ሊሱ በመጪው ጥቅምት ወር ላይ በሚካሄደው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ቻዴማ የተሰኘውን ፓርቲያቸውን ወክለው ለመወዳደር ማሸነፋቸው ተገለፀ።
ፖለቲከኛው ከሦስት ዓመታት በፊት መስከረም ወር ላይ በዋና መዲናዋ ዶዶማ ከተፈፀመባቸው የግድያ ሙከራ ተርፈው ከአገር ወጥተው ነበር።
ባቀኑበት ቤልጂየም ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ካጋጠማቸው ጉዳት ካገገሙ በኋላ ነበር ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አገራቸው የተመለሱት።
በዚህ ሁሉ ያለፉት ፖለቲከኛው አሁን አገሪቷን እየመሩ ያሉትን ፕሬዝደንት ማጉፋሊን ይገዳደራሉ ተብሏል።
በእጩነት መቅረባቸውም ፖለቲከኛው ከተፎካካሪያቸው ጋር በምርጫው ለመወዳደር አቅም እንዳላቸው ያሳየ እንደሆነ ተገጿል።
ፖለቲከኛው በፕሬዝደንትነት ለመወዳደር የታጩት ከፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት 442 አባላት ውስጥ የ405 አባላት ይሁንታን በማግኘት ነው።
ተፎካካሪያቸው የቀድሞው የቱሪዝም ሚኒስተር ላዛሮ ንያላንዱ ደግሞ ያገኙት 36 ድምፅ ብቻ ነበር።
ተቃዋሚ ፖሊቲከኛው ቱንዱ ላላፉት አራት ዓመታት ፕሬዝደንት ማጉፋሊን በድፍረት በመተቸት ይታወቃሉ።
በርካታ ደጋፊዎች እንዳሏቸው የተገለፀ ሲሆን ጥቅምት ላይ በሚካሄደው ምርጫም ከደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ ታንዛኒያ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ፖለቲካውን በበላይነት የያዘው ቻማቻ ማፒንዱዚ ፓርቲን ለማሸነፍ ይህ በቂ ይሆን ሲሉ የሚጠይቁት በርካቶች ናቸው።
የፖለቲከኛው የፕሬዝደንት እጩነት በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ማክሰኞ ዕለት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።