ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዚምባብዌ ሆስፒታል በአንድ ምሽት ሰባት አራስ ሕፃናት መሞታቸው ተነገረ
በዚምባብዌ ዋና መዲና ሃራሬ በሚገኝ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል በአንድ ምሽት ሰባት አራስ ሕፃናት መሞታቸው ተገለፀ።
ሕፃናቱ ለህልፈት የተዳረጉት የሆስፒታሉ ነርሶች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ አድማ ላይ ስለነበሩና በሆስፒታሉ በተፈጠረ መጨናነቅ እንደሆነ ተነግሯል።
ለማዋለጃ ክፍሉ ቅርበት ያላቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ዶክተሮች የህፃናቱን መሞት ለቢቢሲ አረጋግጠው ሕፃናቱ የተወለዱት ሰኞ ዕለት በቀዶ ሕክምና እንደነበር ተናግረዋል።
በዚያን ምሽት ስምንት ሕፃናት መወለዳቸውን ጠቅሰው ከስምንቱ ሰባቱ ሞተው እንደተወለዱ አክለዋል።
የማዋለጃ ክፍሉ በጣም የተጨናነቀ በመሆኑ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል ያሉት ዶክተሮቹ፤ ይህ ያለውን ከፍተኛ ችግር የሚያሳይ ክስተት ነው ብለዋል።
የአራስ ሕፃናቱን የሞት ዜና በመጀመሪያ ያወጡት ዶ/ር ፒተር ማጎምቤይ ሲሆኑ "ያልተወለዱ ሕፃናትን ጨምሮ ወደ ፊታችንን እየተነጠቅን ነው፤ እባካችሁ ዘረፋውን አቁሙ" ሲሉ ነበር ዶ/ሩ በትዊተር ገፃቸው አሳዛኙን ዜና ያሰፈሩት።
ሁለቱ ነፍሰ ጡር እናቶች በእርግዝና በሚፈጠር ውስብስብ የጤና ችግር ያለክትትል ለቀናት በሆስፒታሉ እንዲቆዩ የተተው ሲሆን፤ የተደረገላቸው ሕክምናም በጣም የዘገየ እንደነበር ከዶክተሮቹ አንዱ ተናግሯል።
" ሁለቱ እናቶች ባጋጠማቸው ውስብስብ የወሊድ ችግር ሳቢያ ቀዶ ሕክምና ሊሰራላቸው የሚገባው ቀድሞ ነበር፤ ቀዶ ሕክምናው ያስፈለጋቸው በምጥ መውለድ ባለመቻላቸው ነበር፤ ነገር ግን በጊዜ አልተሰራላቸውም፤ ረፍዷል " ብሏል።
ሌላኛው ዶክተር በበኩሉ "ይህ የተለየ ክስተት አይደለም። በየቀኑ የሚያጋጥም ነው፤ ማድረግ የምንችለው ሲሞቱ ማየት ብቻ ነው ፤ ይህ ለቤተሰብና ለጀማሪ ዶክተሮች ስቃይ ነው" ብሏል።
ዶክተሮቹ በሆስፒታሉ ውስጥ የመድሃኒት ፣ የደም አቅርቦት እንዲሁም የበሽታ መከላከያ የሕክምና ግብዓት አለመኖሩን ተናግረዋል።
በወቅቱ ነርሶች የኮሮናቫይረስ መከላከያ የሕክምና ግብዓት እጥረቶች መኖራቸውን ተከትሎ አድማ ላይ እንደነበሩ የገለፁት ዶክተሮቹ፤ በወቅቱ ያሉት ዶክተሮችም በሥራ ተጨናንቀው ነበር ብለዋል።
" ጥቂት ዶክተሮችና ነርሶች ነበሩ፤ ዶክተሮቹ የሚችሉትን አደረጉ ግን ተዳክመው ነበር፤ ጀማሪ ዶክተሮች ደግሞ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥሙ ውስብስብ የጤና ችግሮችን በቀላሉ ማወቅ አይችሉም" ይላሉ እኝህ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዶክተሮች።
ከኮቪድ -19፣ ከበሽታ መከላከያ የሕክምና ግብዓቶች እጥረት፣ ከዋጋ ግሽበትና ከኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ በሃራሬ የሚገኙ በርካታ ክሊኒኮችም ተዘግተዋል።
ይህም ነፍሰጡር ሴቶች በከተማው ወደሚገኘው ትልቅ የመንግሥት ሆስፒታል ብቻ እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል። ሆስፒታሎቹም ይህንን ለማስተናገድ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል።
"ያለው ሁኔታው በጣም አስከፊ ነው" ሲል አንዱ ዶክተር ያለውን ሁኔታ አስረድቷል።
የዚምባብዌ የማህፀንና ፅንስ ሐኪሞች ማህበር ባወጣው መግለጫ ሁኔታውን አሳዛኝ እና ከአስከፊነት በላይ ነው ሲሉ ገልፀውታል።
" ሴቶች እየተሰቃዩ ነው። ባለድርሻ አካላት ፣ መንግሥት ፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ ሲቪል ሶሳይቲ እና ግለሰቦች ድምፅ የሌላቸውን እናቶችና ሕፃናት ለማዳን የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ እናምናለን" ብለዋል በመግለጫቸው።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ከሆነ በዚምባብዌ እስካሁን ወደ 2 ሺህ 800 የሚጠጉ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን 40 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።
በአገሪቷ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት ከተላቀቀች ጀምሮ አገሪቷን እየመራ ያለውን ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲን የሚቃወም ሰልፍ አርብ ይኖራል በሚል ውጥረት ነግሷል።