አሜሪካ በቻይና የሚገኘው ቆንስላዋን ለቅቃ ወጣች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በቻይናዋ ቼንግዱ ከተማ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ ዲፕሎማቲክ አባላት የተቀመጠላቸው የ72 ሰአት ገደብ በማለቁ ቅጥር ግቢውን ለቅቀው መሄዳቸው ተሰምቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ ሂውስተን የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ ከዘጋች በኋላ ነው ቻይናም በምላሹ የአሜሪካ ቆንስላ አንዲዘጋ ያዘዘችው።

ልክ ሰኞ ዕለት የሚያበቃው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት የቆንስላው ሰራተኞች ግቢውን ሲለቅቁ ታይተዋል። የአሜሪካ ባንዲራም እንዲወርድ ተደርጓል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደግሞ ቀነ ገደቡ ካለቀ በኋላ የቻይና ሰራተኞች ቅጥር ግቢውን ተቆጣጥረውታል ብሏል።

የአሜሪካ ቆንስላ መዘጋቱን ተከትሎ በርካታ ቻይናውያን በአካባቢው በመሰባሰብ የአገራቸውን ባንዲራን ሲያውለብቡና ፎቶ ሲነሱም ተስተውዋል።

አሜሪካ በቴክሳስ ሂውስተን ከተማ የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ የዘጋችው ባሳለፍነው አርብ ሲሆን፣ በወቅቱም ቤጂንግ የአሜሪካ ውሳኔ “ፖለቲካዊ ፍላጎት የታየበት” ነው ብላለች።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ከዚህ ውሳኔ የተደረሰው “የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ነው” ብሏል።

ውሳኔውን ተከትሎ የቻይና የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በበኩላቸው አሜሪካ ቆንስላው እንዲዘጋ መወሰኗ “እጅጉን የሚያስቆጣ ነው፤ ለውሳኔው ትክክለኛነት መከራከሪያ ማቅረብ እንኳ አያስችልም” ብለው ነበር።

በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው ውጥረት በተለያዩ ምክንያቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያየለ መጥቷል።

• የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቤጂንግ መንግሥት ጋር በንግግር እንዲሁም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ይጋጫል

• በሆንግ ኮንግ ጉዳዮችም የአሜሪካ መንግስት ከቻይና ጋር ሲነታረክ ይስተዋላል

• እንዲሁም በርካታ ቻይናውያንን በቪዛ ማጭበርበርና በቻይና መከላከያ ሰራዊት ስላላቸው ሚና ዋሽተዋል በማለት አሜሪካ በቁጥጥር ስር አውላቸዋለች

የቻይናው ሲሲቲቪ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ በርካታ የቆንስላው ሰራተኞች ቅጥር ግቢውን ለቅቀው ሲሄዱ የሚያሳይ ሲሆን፣ ፖሊስ ደግሞ በአካባቢው የተሰበሰቡ ሰዎችን ስርአት ለማስያዝ ሲሞክር ተስተውሏል።

ሁኔታውን በርቀት ሲከታሉ የነበሩ ቻይናውያንም አንድ ሰራተኞችን የጫነ መኪና ሲወጣ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሂውስተን የቻይና ቆንስላ ሰራተኞችም ግቢውን ለቅቀው ሲወጡ በአካባቢው ሰዎች ተመሳሳይ ተቃውሞና ማንጓጠጥ አጋጥሟቸው ነበር።

አሜሪካ በቼንግዱ የሚገኘው ቆንስላዋ መዘጋቱን ተከትሎ በቻይና ያሏት የቆንስላዎች ቁጥር ወደ አራት የወረደ ሲሆን በዋና ከተማዋ ቤዢንግ ደግሞ ኤምባሲው ይገኛል።

ቻይናም ብትሆን በሂውስተን የነበረው ቆንስላ ቢዘጋባትም ሌሎች ተጨማሪ አራት ቆንስላዎች አሏት። በዋሽንግተን ዲሲ ደግሞ ዋናው ኤምባሲ ይገኛል።