የአሜሪካ አምባሳደር ጺም ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ አስነሳ

አምባሳደር ሃሪ ከነጺማቸውና ጺማቸውን ተላጭተው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አምባሳደር ሃሪ ከነጺማቸውና ጺማቸውን ተላጭተው
ታትሟል

ከሰሞኑ ኮሪያ ውስጥ ጺም ለዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ምክንያት ሆኗል።

አምባሳደር ሃሪ ሃሪስ በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ አምባሳደር ናቸው።

በእንግሊዝኛ ሞስታሽ የሚባለው ከላይኛው ከንፈር በላይ የሚገኘው ጺማቸው ከበድ ያለ ጭቅጭቅ ያስነሳባቸው አምባሳደሩ በዋና ከተማዋ ሴኡል ወደሚገኝ አንድ ጸጉር ቤት ሄደው ሙልጭ ተደርገው ተነስተውታል።

አምባሳደሩ ይህንን ጺማቸውን እስከዛሬ ሳይስተካከሉት ለምን እንደቀሩ ሲጠየቁ "ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ጭምብል ስለማጠልቅ ተመችቶኝ ስለነበረ ነው" ብለዋል።

ሂትለር እና ሳዳም ሁሴን በዚህ የሞስታሽ ጺማቸው ይበልጥ ይታወቃሉ። የአሜሪካ አምባሳደር ጺም ጉዳይ ሊሆን የቻለው ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጃፓንና በኮሪያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ንፋስ ከገባ በኋላ ነው።

"አሁን ቆንጆ ሆኛለሁ" ብለዋል አምባሳደሩ ጺማቸውን ከተቆረጡ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት ተንቀሳቃሽ ምሥል።

ጺማቸው ለምን ችግር ሆኖ ታየ?

የአምባሳደሩ ጺም በዚህ ደረጃ አቧራ ያስነሳው ደቡብ ኮሪያ በጃፓን ቅኝ ግዛት ስር ለ35 ዓመታት ከመቆየቷ ጋር ተያይዞ ነው። ደቡብ ኮሪያ እንደ ፈረንጆቹ ከ1910 እስከ 1945 ድረስ ነበር በጃፓን ስር የነበረቸው።

ታዲያ የአምባሳደሩ ጺምና የጃፓን ቅኝ ግዛትን ምን አገናኛቸው ብለው ጠይቀው ይሆናል።

ነገሩ ወዲህ ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን የጃፓን ገዢዎች ደቡብ ኮሪያን ሲያቀኑ የከንፈር ጢማቸውን ያስረዝሙ ነበር።

ይህ መጥፎ ትዝታ በአምባሳደሩ ጺም ምክንያት ዳግም በመቀስቀሱ ነው ውዝግቡ የተነሳው።

አምባሳደር ሃሪስ የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መልካም ባልሆነበት ሰዓት የአፍንጫ ግርጌ ጺማቸውን አስረዝመው መታየታቸው ነው ነገሩን ያባባሰው።

አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮቿን በደቡብ ኮሪያ አስፍራለች። ይህም ከሰሜን ኮሪያ የሚሰነዘር ጥቃት ካለ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት በሚል ነው።

ሚስተር ሃሪስ ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት ደቡብ ኮሪያ በወታደራዊ ወጪዋ ላይ ጨከን ብላ ጭማሪ እንድታደርግ አስተያየት ሰጥተው ነበር። ይህም አስተያየታቸው በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስ ምክንያት ሆኖ ነበር።

አምባሳደሩ ከዚህ ቀደም በዚህ ንግግራቸው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ዘራቸው በግማሽ ከጃፓን ስለሚመዘዝም ጭምር ረዥሙ ጺማቸው ለተራዘመ ውዝግብ ምክንያት ሆነዋል።

ባለፈው ታኅሣሥ 'ኮሪያን ታይምስ' የተባለው ጋዜጣ ባሰፈረው ርዕሰ አንቀጹ "የአምባሳደሩ ጺም አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ለደቡብ ኮሪያ ያላትን ንቀት የገለጸችበት ነው" ሲል ጽፎ ነበር።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጦረኛ የጃፓን ጄኔራሎች የነበሩት ሃይዲ ቶጆ፣ ሳዳኦ አራኪ እና ሹንኩሩ ሃታ ሁሉም አሁን አምባሳደሩ እንደነበራቸው ዓይነት ሞስታሽ ጺም ነበራቸው። መለያቸውም ተደርጎ ይታሰባል።

ነገር ግን አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የአምባሳደሩ ዓይነት ጺም ማስረዘም በዘመኑ በኮሪያዊያን ገዢዎች ጭምር የተለመደ ነበር።

አምባሳደር ሃሪስ በበኩላቸው የአፍንጫ ግርጌ ጺማቸው ይህን ያህል ውዝግብ ሊቀሰቅስ የቻለው እናታቸው ጃፓናዊት ስለሆነች ብቻ ነው።

የአሜሪካ አምባሳደር ሃሪስ አባታቸው አሜሪካዊ ሲሆኑ የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባልም ነበሩ።