ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን በግዛቷ የተከሰከሰውን የዩክሬን አውሮፕላን የመረጃ ሰንዱቅ ለፈረንሳይ ላከች
ኢራን በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ በቴህራን የተከሰከሰውንና ንብረትነቱ የዩክሬን የሆነውን የመንገደኞች አውሮፕላን የመረጃ ሳንዱቅ (ብላክ ቦክስ) ለፈረንሳይ መላኳን አስታወቀች።
የመንገደኞች አውሮፕላኑ አደጋ በሁለት ሚሳይሎች ተመትቶ የተከሰከሰ ሲሆን ተሳፍረው የነበሩ 176 ሰዎችም መሞታቸው ይታወሳል።
የኢራኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር እንዳሉት የመረጃ ሳንዱቁ (ብላክ ቦክስ) አርብ ዕለት ወደ ፓሪስ የተላከ ሲሆን ሰኞ ይነበባል ብለዋል።
ኢራን መጀመሪያ ላይ ለተፈጠረው አደጋ ኃላፊነቱን ባለመውሰዷ ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ይሁን እንጅ የምዕራባዊያን የደህንነት ባለሥልጣናት በአደጋው ኢራን እጇ እንዳለበት ከጠቆመ በኋላ ኃላፊነቱን ወስዳለች።
በዚህም የዩክሬን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ አውሮፕላን በስህተት በሚሳይል ተመትቶ መውደቁን ኢራን አምናለች። ፕሬዚደንት ሐሰን ሩሃኒም ክስተቱን " ይቅርታ የማያሰጥ ስህተት" ብለውታል።
አደጋው ከመድረሱ ከሰዓታት በፊትም የኢራን አየር ኃይል በተጠንቀቅ ላይ እንደነበር ተገልጿል።
ኢራን አሜሪካ በባግዳድ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በፈፀመችው ጥቃት ለተገደለው የኢራን ከፍተኛ ጀነራል ቃሲም ሶሌኢማኒ አፀፋ ለመመለስ በኢራን የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች መኖሪያ ሰፈር ላይ የሚሳዔል ድብደባ አካሂዳለች።
ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ለምን አስፈላጊ ሆነ?
ኢራን ከዚህ ቀደም ወሳኝ የበረራ መረጃዎችን የያዘውን ጥቁሩን ሳጥን መገኘቱን ይፋ ለማድረግ ዘግይታ ነበር። ይህም ዜጎቻቸውን በአደጋው ባጡ አገራት መካከል አለመስማማት ፈጥሮ ነበር።
በዓለም አቀፍ አቪየሽን ሕግ መሰረት ኢራን ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት የሆነውን ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራ የመምራት መብት አላት።
አምራቾችም በአውሮፕላን መከስከስ አደጋ ምርመራው ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በጣም ጥቂት ባለሙያዎች ብቻ የመረጃ ሳንዱቁ ያዘውን የመረዳትና የማብራራት ብቃቱ አላቸው።
ኢራን ጥቁር ሳጥኑን አውሮፕላን አምራቹ ኩባንያ ለተቀመጠበት አሜሪካ አልሰጥም ብላ ቆይታለች።
አሁን ላይ ግን በፈረንሳይ ባለሙያዎች እንዲመረመር የተላከ ሲሆን፤ በአደጋው 55 ዜጎቿን ያጣችው ካናዳ እና ዩክሬን በምርመራው ላይ የሚሳተፉ የራሳቸውን ባለሙያዎች እንደሚልኩ ተናግረዋል።
ኢራን ስለተፈጠረው ምን ብላ ነበር?
ኢራን በአደጋው ላይ ምርመራ ያደረገች ሲሆን ባለፈው ሳምንት በአገሪቷ ሲቪል አቪየሽን ድርጅት ያወጣው ሪፖርት "የሰዎች ስህተት" እና "ደካማ የሆነ ወታደራዊ ኮሚዩኒኬሽን" የአደጋው ምክንያት እንደሆነ አትቷል።
ይሁን እንጅ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስቸኳይ መግለጫ እንደሆነ በመግለፅ፤ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ዓለም አቀፍ የምርመራ ውጤቱን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ባለፈው ወር የኢራን ባለሥልጣናት አደጋውን ተከትሎ ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቀዋል።
ኢራን በአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ስትፈፅም የበረራ ክልሉን ነፃ አላደረገችም በሚል ትወነጀላለች።
በቅርቡ የካናዳው ሲቢሲ ኒውስ አገኘሁት ባለው የተቀዳ የድምፅ ማስረጃ አገሪቷ በጦር ሰፈሩ ላይ ጥቃት የመፈፀም ሃሳቧ እንዳይታወቅ የአየር ክልሉ ክፍት መሆኑን አመልክቷል ብሏል።
የድምፅ መረጃው በአደጋው ሕይወቱን ካጣ ግለሰብ ቤተሰብ የኢራንን የአደጋ ምርምራ ሲመሩ ከነበሩት ሃሰን ሬዜፋር ጋር የተደረገ ንግግር ነው።
የኢራኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሞህሰን ባሃርቫንድ የድምፅ መረጃው እንደ ማስረጃ ሊጠቅም አይችልም በማለት ድምፁን ውድቅ አድርገውታል።