የጂሃዲስት ፖሊስ አዛዡ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀረበ

የፎቶው ባለመብት, ICC
በማሊዋ ቲምቡክቱ ከተማ የጂሃዲስት ፖሊስ አዛዥ የነበረው ግለሰብ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀረበ።
አል ሃሰን አግ አብል አዚዝ አግ ሞሐመድ አግ መሃሙድ የተባሉት ተከሳሽ በቲምቡክቱ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ሰቃይ አድርሷል እንዲሁም ጾታዊ በደሎችን ፈጽሟል የሚል ክስ ተመስርቶበታል።
ግለሰቡ በማሊዋ ቲምቡክቱ ከተማ ጥብቅ የእስልምና ሥርዓት ያሰፈነው የጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን አባል ነበረ ተብሏል። አል ሃሰን በከተማዋ የነበሩ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲፍርሱ አድርጓል የሚል ክስም ቀርቦበታል።
አል ሃሰን በማሊ ባለስልጣናት ለፍርድ ቤቱ ተላልፎ የተሰጠው ከአምስት ዓመታት በፊት ቲምቡክቱ ከተማን ነጻ ለማውጣት የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መንግሥት ጋር ቲምቡክቱን ነጻ ለማውጣት ከዘመቱ በኋላ ነበር።
አል ሃሰን የአንሳር ዲን ሚሊሻ ቡደን አባል ሳለ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸመ ተመዝግቧል። ይህ ቡድን (እአአ) 2012 ቲምቡክቱ ከተማን ተቆጣጥሮ ነበር።
አቃቢ ሕጓ ፋቱ ቤንሱዳ ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አንሳር ዲን ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ እንደነበረ የተናገሩ ሲሆን፤ ጨምረውም በቲምቡክሩ "ሁሉም ነገር ተከልክሎ ነበር" ሲሉ አስረድተዋል።
ሴቶች እጆቻቸውን ጭምር ጓንት በማድረግ ካልሸፈኑ በአደባባይ እንዲገረፉ ይደረጉ እንደነበረ አቃቢ ሕጓ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም አል ሃሰን ሴቶች ለሚሊሻዎች እንዲዳሩ ያስገድዱ አንደነበረ ተጠቁሟል።
ቲምቡክቱ ከጭቃ እና ከእንጨት የተሰሩ ግንባታዎች በስፋት ትታወቃለች።
ከ13ኛው እሰከ 17ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የእስልምና አስተምህሮ ማዕከል የነበረችው ቲምቡክቱ (እአአ) 1988 ላይ በዩኔስኮ የዓለም ቀርስነት ተመዝግባም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters












