ኮሮናቫይረስ፡ በኮሮናቫይረስ ታማሚ ብዛት ህንድ ሩሲያን በለጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት ከ24 ሺህ በላይ የኮሮናቫይረስ ታማሚ ያስመዘገበች ሲሆን ይህም በድምሩ ከሩሲያ በላይ ታማሚ ያላት አገር እንድትሆን አድርጓታል።
ሕንድ አሁን ላይ 697 ሺህ 413 የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ሲኖሯት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሦስተኛዋ አገርም ሆናለች። 19 ሺህ 693 ዜጎቿ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
አዲሱ ከፍተኛ የቫይረሱ ስርጭት በአገሪቱ ደቡባዊ ግዛቶች በብዛት የተስተዋለ ሲሆን፤ ቴላንጋና፣ ታሚል ናዱ እና ካርናታካ የተባሉት ግዛቶች በከፍተኛ ደረጃ የተጠቁት ግዛቶች ናቸው።
ሕንድ ከአንድ ሱቆችን፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና ቢሮዎችን ክፍት ያደረገችው ከአንድ ወር በፊት ነው።
ባለፉት ሦስት ቀናት በሕንድ ዕለታዊ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከ20 ሺህ በላይ ሆኗል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያመለክተው ሕንድ በታማሚ ብዛት ከዓለም ሦስተኛ ብትሆንም በሟች ብዛት ግን ስምንተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ደቡባዊ የሕንድ ግዛቶች ቀደም ሲል ወደቦቻቸው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርገው የቫይረሱን ስርጭት በመግታት የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የእገዳውን መላላትን ተከትሎ ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነባቸው ነው።
ሕንድ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ ዝግ ያደረገችው ገና የቫይረሱ ታማሚዎች ቁጥር በመቶዎች በነበረበት ወቅት መጋቢት ላይ ነበር።
ምንም እንኳ የቫይረሱ ስርጭት ቢጨምርም የምጣኔ ሃብቱን ለማነቃቃት በሚል በሰኔ ወር ላይ እገዳውን ማላላት ጀምራለች።
ባለሙያዎች እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመዘገበው 4.7 በመቶ የሞት መጠን አኳያ ስትታይ ሕንድ የሞት መጠኗ 2.4 በመቶ ብቻ በመሆኑ እንደ መልካም አጋጣሚ ተወስዶላታል።
ሌላኛው ለሕንድ አበረታች ነገር ደግሞ 60 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ታማሚዎች ማገገም መቻላቸው ነው።
አሁን ደካማውን የአገሪቱን የጤና ተቋም እየተፈታተነ ያለው ቀሪው 36 በመቶ የሚሆነው የታማሚ ብዛት ነው።
መዲናዋ ኒው ደልሂንና ሙምባይን ጨምሮ በትልልቅ ከተሞች ህሙማን የህክምና እርዳታ ተነፍገው ለሞት ሲዳረጉ ከዚህም ባለፈ በኅብረተሰቡ ላይ ቁጣን እስከመቀስቀስ ደርሷል።
በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች የምርመራ ቁጥር የጨመረ ሲሆን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ዕለታዊ ምርመራው እስከ 250 ሺህ መድረሱን ዘግበዋል።
በአሁኑ ወቅት በሕንድ በከፊል እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የጎዳና ላይ ሥራዎች፣ ምግብ ቤቶች ሥራ የጀመሩ ሲሆን ሠራተኞችም ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል።
በዚህ ወቅት በሕንድ የቫይረሱ ታማሚ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩ ምናልባትም ሙያተኞች ሕንድ ከፍተኛውን ቁጥር የምታስመዘግበው በሐምሌና ነሐሴ መካከል ነው ያሉት ጋር የሚገጣጠም ሳይሆን አይቀርም።












