ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው በኮሮናቫይረስ ላይ "አንፀባራቂ ድል" ማስመዝገቧን ተናገሩ

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የሰሜን ኮርያ መሪ የሆኑት ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው የኮሮናቫይረስን ስርጭት በመከላከል ረገድ "አንጸባራቂ ድል" ማስመዝገቧን በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ ንግራቸው ላይ ሲሉ ተሰምተዋል።

ፕሬዝዳንት ኪም በፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ" አስከፊው ቫይረስ ወደ አገራችን እንዳይገባ ተከላክለናል እንዲሁም ያለውን የተረጋጋ ሁኔታ አስቀጥለናል" ብለዋል።

ቫይረሱ በመላው ዓለም መሰራጨት ከጀመረበት ከስድስት ወር በፊት ጀምሮ ሰሜን ኮርያ ድንበሯን ሙሉ በሙሉ ዘግታ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አድርጋ ነበር።

በርካታ የጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ይህ የሚቻል አይደለም ቢሉም ሰሜን ኮርያ ግን እስካሁን ድረስ ኮቪድ-19 ድንበሬን ተሻግሮ አልገባም ስትል ተናግራለች።

ኪም እንዳሉት ሐሙስ እለት በነበራቸው የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ አገሪቱ ላለፉት ስድስት ወራት የቆየችበትን የወረርሽኝ መከላከል የአስቸኳይ ጊዜ ስራ መገምገማቸውን ተናግረዋል። አክለውም በአገሪቱ የተገኘው ቫይረሱን የመቆጣጣር ስኬት "በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት አመራር ነው" ሲሉ አንቆለጳጵሰዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቫይረሱ በጎረቤት አገራት መኖሩን በመግለጽ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ መመሪያዎች መላላት "የማይታሰቡና የማይቀለበሱ ቀውሶችን " ያስከትላል በማለት ሲናገሩ በቴሌቭዢን ላይ ታይቷል።

እስካሁን ድረስ በሰሜን ኮሪያ ያለውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት መጠን አንድም ገለልተኛ አካል ይህ ነው ብሎ አልተናገረም።

አገሪቱ ከጎርጎሳውያኑ ታህሳስ 30 ጀምሮ ዝግ ስትሆን በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሲገቡና ሲወጡ ታይተዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይመስቀል ድርጅት በድንበር አካባቢ የቫይረሱ መከላከል ላይ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች ያሉት ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ያልተረጋገጡ የኮቪድ-19 ሕሙማን ሪፖርቶች መኖራቸውን ይናገራል።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዋና ከተማዋ ህይወት እንደቀድሞው ቀጥሎ ታይቷል።

እውነታው ምንም ይሁን ምን ፒዮንግያንግ ኮቪድ-19ን በመከላከል ላይ ድል መቀዳጀቷን ለዓለም ማሳየት የፈለገች ይመስላል።

በአገር ውስጥ ኪም ጆንግ ኡን ቫይረሱ የአገራቸውን ድንበር እንዳይሻገር ለማድረግ ከወሰዱት ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ አንጻር ድል መተነዋል ማለታቸው ለሕዝቡ ጠንካራ መልእክት አለው ያሉ ተንታኞች አሉ።።

በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ሰሜን ኮርያ ድንበሯን በመዝጋት፣ ከዚያም በኋላ በዋና ከተማዋ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጪ ዜጎችን ወደ ለይቶ ማቆያ በማስገባት ቫይረሱን ለመከላከል እርምጃ ወስዳለች።

የራሷ ዜጎችንም ቢሆን ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አድርጋለች።

በአሁን ሰአት ትምህርት ቤቶች ክፍት ቢሆንም ነገር ግን መሰብሰብ ሲከለከል እንዲሁም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ግዴታ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ድረስ 922 ሰዎችን የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማድረግ ሁሉም ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጧን ገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ከቻይና ጋር ረዥም ድንበር የምትጋራ ሲሆን እስካሁን አንድም ሰው በቫይረሱ አልተያዘብኝም ማለቷን የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በጥርጣሬ እያየው ይገኛል።

ኮሮና
Banner