ታንዛኒያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ተመደበች

የገበያ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

ታንዛኒያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ መግባቷ ተገለፀ ። ይህ የሆነው የዓለም ባንክ የዓለም አገራትን ምጣኔ ሐብት ከተመለከተ በኋላ ነው።

ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ታንዛኒያ ከዚህ ዝርዝር ውስጥ የገባችው፤ በአገሪቷ ያለው የአንድ ሰው ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ1006 እና 3955 ዶላር መካከል በመሆኑ ነው።

የአንድ ሰው ዓመታዊ አማካይ ነፍስ ወከፍ ገቢ አገሪቷ የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ የዶላር ዋጋ ለሕዝብ ብዛቷ በማካፈል የሚገኝ ስሌት ነው።

ባለፈው ዓመት የታንዛኒያ ኢኮኖሚ በ6.8 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት በፊትም 7 በመቶ እድገት አሳይቶ ነበር። ይህም በዓለማችን ፈጣኑ የኢኮኖሚ እድገት ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ነው።

እንደ አጥኚዎቹ ከሆነ ይህ የምጣኔ ሐብት እድገት ለአስር ዓመታት የቀጠለ ሲሆን ፕሬዚደንት ጆን ማጉፉሊም ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላም እንደቀጠ ይገኛል።

አገሪቷ በቀጠናው ከፍተኛ ምጣኔ ሐብት ያላት ሁለተኛዋ አገር ሆናለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አፍሪካ መዛመቱን ተከትሎ ሚያዚያ ወር ላይ የዓለም ባንክ ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮቪድ-19 ምክንያት የኢኮኖሚ ድቀት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ተንብዮ ነበር።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት በዚህ ዓመት ብቻ በ2.1 በመቶ የሚጎዳ ሲሆን ይህ ጉዳት እስከ 5.1 ድረስ ሊደርስ ይችላል ብሏል።

የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አበዳሪ አገራት ለአፍሪካ እዳቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያራዝሙ እና አገራት ያላቸውን ገንዘብ ወደ ሕይወት ማዳንና ኑሮን ማሻሻል ላይ ማዋል እንዲችሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በአፍሪካ በምጣኔ ሃብታቸው ግዙፍ የሆኑት ናይጄሪያና አንጎላ በወረርሽኙ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መውረድ ምጣኔ ሃብታቸው ክፉኛ ከተጎዳ አገራት መካከል ይገኙበታል። ደቡብ አፍሪካም ብትሆን የማዕድን ገቢዋ አሽቆልቁሎባታል።

ኮሮና
Banner