በኡጋንዳ "ጉቦ የተጠየቀ" የሞተር ሳይክል አሽከረካሪ ራሱን አጠፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡጋንዳ ውስጥ የ29 ዓመቱ የሞተርሳይክል አሽከርካሪ ራሱ ላይ እሳት በመለኮስ ሕይወቱን ማጥፋቱ ተገለፀ።
አሽከርካሪው ራሱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ እሳት የለኮሰው ሞተር ሳይክሉ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎበት ለማስለቀቅ በሄደበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ነው ተብሏል።
ግለሰቡ ሁሴን ዋላጉምቤ የሚባል ሲሆን፤ ሞተርሳይክሉ የተያዘበት ከዋና ከተማዋ ካምፓላ 134 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በደቡብ ምዕራብ ማሳካ ከተማ ሰኞ እለት ነበር።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ሥርጭት ለመከላከል በወጣው መመሪያ መሰረት መንግሥት የሞተር ሳይክል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡትን (በእነርሱ አጠራር ቦዳ ቦዳ) ሰዎችን እንዳያመላልሱ ከልክሎ ነበር።
ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሞተርሳይክሎች መንቀሳቀስ የተፈቀደላቸው ከንጋቱ 12፡30 እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ብቻ ሲሆን ማመላለስ የሚችሉትም እቃ ብቻ ነው ተብሏል።
እንደ ፖሊስ ሪፖርት ከሆነ ዋላጉምቤ ሞተር ሳይክሉን ለጓደኛው ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ጓደኛው ሰው ጭኖ በመገኘቱ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ግለሰቡ ፖሊስ ጣቢያ ሞተር ሳይክሉን ለማስለቀቅ ቢመላለስም ፖሊስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተስፋ ቆርጦ ነበር።
ሐሙስ እለት በፖሊስ ጣቢያው በአንድ ክፍል ውስጥ በመግባት ራሱ ላይ ከቆለፈ በኋላ በጠርሙስ ተቀድቶ የተቀመጠ ነዳጅ በማንሳት ራሱ ላይ አርከፍክፎ እሳት ለኩሷል።
በፖሊስ ጣቢያው የነበሩ ፖሊሶች እሳቱን ለማጥፋት ውሃ በመድፋት መረባረባቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ አብሮት የነበረ ፖሊስ ቀላል ቃጠሎ ያጋጠመው ሲሆን በርካታ ሰነዶችና ኮምፒውተሮች በቃጠሎ ወድመዋል።
አንዳንድ ሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች የፖሊስ ባልደረባው ሞተር ሳይክሉን ለመልቀቅ ግለሰቡን 40 ዶላር ጉቦ እንዲሰጠው ጠይቆት ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
ግለሰቡ ራሱን ካጠፋ በኋላ የክልሉ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፖል ካንጋቬ በአጠቃላይ በትራፊክ ፖሊስ ክፍሉ ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልፀዋል።
አክለውም የፖሊስ ኃይሉ የሙያ ሥነ ምግባር ክፍል የፖሊስ ባልደረባው ጉቦ ጠይቆት ነበር በሚል የቀረበውን ውንጀላ ይመረምራል ብለዋል።
በኡጋንዳ በርካታ ወጣቶች በሞተር ሳይክል ሰው እና እቃ የማጓጓዝ አገልግሎት በመስጠት ገቢ ያገኛሉ።
የኡጋንዳ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ጥሏቸው የነበሩትን በርካታ ገደቦች ቢያነሳም በሞተር ሳይክል አገልግሎት ላይ የጣለውን ገደብ ግን እስካሁን ድረስ አላነሳም።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ሰዎችን በሞተር ሳይክል ማጓጓዝ የበለጠ የቫይረሱን ስርጭት ያስፋፋዋል ብለው ነበር።
ኡጋንዳ እስካሁን ድረስ ባደረገችው የኮሮናቫይረስ ምርመራ 900 ሰዎች መያዛቸው ሲታወቅ ከእነዚህ መካከል 847 ሰዎች አገግመዋል። ምንም ዓይነት ሞት አልተመዘገበም።
በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የከባድ መኪና አሽከርካሪዎችና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው።














