በእንግሊዝ ሬዲንግ ከተማ በስለት ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ "በኤምአይ5 ይታወቅ ነበር" ተባለ

ኻይሪ ሳዳላህ የማህበራዊ ሚዲያ ምስል
ታትሟል

እንግሊዝ ውስጥ በሬዲንግ ከተማ መናፈሻ በሦስት ሰዎች ግድያ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ኤምአይ5 በተባለው የአገሪቱ የደኅንነት ተቋም ክትትል ውስጥ እንደነበር ምንጮች ገለፁ።

የ25 ዓመቱ ወጣት ኻይሪ ሳዳላህ ቅዳሜ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ በደረሰው የሽብር ጥቃት ሌላ የሚፈልጉት ሰው እንደሌለ አስታውቋል።

ለቢቢሲ መረጃውን ያቀበሉ ሰዎች እንዳሉት ግለሰቡ ከሊቢያ የመጣ ሲሆን በኤምአይ5 እይታ ውስጥ የገባው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ቅዳሜ ማታ በመናፈሻ ስፍራው በተፈጸመው ጥቃት "በከፍተኛ ሁኔታ ማዘናቸውን" ገልፀዋል።

የጸረ ሽብር ፖሊስ በበኩሉ የ25 ዓመቱ ወጣት በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሲሆን አሁን ግን በድጋሚ በሽብር ተግባር በቁጥጥር ስር መሆኑን አሳውቋል።

የደኅንነት ምንጮች እንዳሉት ግለሰቡ በደኅንነት ሠራተኞች ትኩረት ውስጥ የገባው ከአገር ውጪ ለመሄድ እቅድ እንደነበረው ከታወቀና ለሽብር ጥቃት ሊሆን ይችላል የሚል መረጃ ከደረሳቸው በኋላ ነው።

በርግጥ ይህ መረጃ ሲመረመር አደጋ ሊያደርስ ወይንም ስጋት ሊፈጥር የሚችል መሆኑን የሚገልጽ የተገኘ ምንም ፍንጭ ሰጪ ነገር የለም።

እስካሁን ድረስ ለተጨማሪ ምርመራ የሚጋብዝ ምንም ክስ አልተመሰረተም።

ፖሊስ ጥቃቱ ሲፈጸም ድርጊቱን በሞባይል ቪዲዮ የቀረጸ ካለ መረጃውን እንዲሰጠው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ለጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች ክብር ሲባል ምስሎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንዳይሰራጩ ጠይቋል።

አንድ በስፍራው የነበረ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቃት ፈጻሚው በመናፈሻው ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች መካከል እየተንቀሳቀሰ ሰዎችን በስለት ለመውጋት እንደሞከረና ወደ እሱም እየሮጠ መምጣቱን ገልጿል።

ሰንደይ ሚረር የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በሰዎች ላይ በስለት ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ አንድ ፖሊስ ታግሎ ከመሬት ላይ ከጣለው በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ቅዳሜ ዕለት የደረሰው ጥቃት የደህንነት ኃላፊዎች "በተናጠል የተፈፀመ" ሲሉ የሚገልጹት ዓይነት ጥቃት ነው የተባለ ሲሆን አንድ ግለሰብ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ብቻውን ወደ ጽንፈንነት የሚቀየርበት ነው ተብሏል።

ከባለፈው ዓመት ህዳር ወር ጀምሮ በዩናይትድ ኪንግደም ባለስልጣናት የሽብር ስጋት ደረጃ መቀነሱን ተገልጾ ነበር። ያም ማለት የሽብር አደጋ ሊከሰት ቢችልም በአስቸኳይ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር እንደማይኖር ነበር የተገለፀው።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሶስት ጥቃቶች የተፈፀሙ ሲሆን ሁለት ሰዎችም ሞተዋል። ሁለቱ ጥቃቶች የተፈፀሙት በተናጠል ግለሰቦች መሆኑም ተገልጿል።

ዛሬ መርማሪ ቡድኖች ተጠርጣሪውን የሚመረምሩ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ጠበብቶች ደግሞ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተጠርጣሪው የነበረውን ግንኙነት፣ ያካሄዳቸውን የስልክ ጥሪዎችና መልዕክቶች ወደ ኋላ ተመልሰው በመመርመር ከጽንፈኞች ጋር የነበረውን ግንኙነት ይመረምራሉ ተብሏል።

የኤም አይ 5 መርማሪዎች ከዚህ በፊት የተዘጉ አልያም ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉ ክሶችን ከዚህ ወንጀል ጋር የሚያገናኛቸው ነገር ካለም ይመለከታሉ።

የተጠርጣሪውን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ምስሎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው ወንጀሉን በተፈፀመ በአምስት ደቂቃ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

የተጠርጣሪው ጓደኛ ለወንጀል መርማሪዎች እንዳስታወቀው ግለሰቡ "እንደማንኛውም ሰው ትሁትና ቀና" ይመስል ነበር ብሏል።