በኮቪድ-19 ምክንያት በክትባቶች ስለተስጓጎሉ በቀን 6 ሺህ ሕጻናት ይሞታሉ

ታትሟል

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወዲህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ሊሞቱ ይችላሉ። የሚሞቱት ታዲያ በኮሮናቫይረስ አይደለም። በሽታው ባመጣው ጣጣ እንጂ።

በብዙ የዓለም ደሀ አገራት ኮቪድ-19 በደቀነው ስጋት የተነሳ ለሌሎች በሽታዎች ይሰጥ የነበረውን የክትባት መርሐ ግብርን አመሳቅቅሎታል፤ አደናቅፎታል።

በትንሹ 68 አገራት ለሕጻናት ይሰጡት የነበረውን መደበኛ የክትባት መርሐግብራቸው በኮቪድ-19 ምክንያት እንደተቋረጠባቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

አገራቱ የክትባት ዘመቻን እንዲያቋርጡ የተመከሩትም በዚህ የዓለም ጤና ድርጅት በራሱ ነው። ምክንያቱም የዘመቻ ክትባት የማኅበረሰብ ጥግግትን ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ለኮሮናቫይረስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል በሚል ስጋት ነው።

ከአንድ በሽታ እድናለሁ ብሎ በሌላ በሽታ መያዝ

በዚህ የወረርሽኝ ዘመን ጥግግት አደጋ እንደሚያመጣ እውን ሆኖ ሳለ በዚያው መጠን መደበኛ ክትባቶች መደናቀፋቸው ደግሞ ዞሮ ዞሮ ለብዙ ሕጻናት ሞት ምክንያት መሆኑ እየተገለጸ ነው።

ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ጉዳዩ አሳስቦናል እያሉ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ ሳቢን የቫክሲን ኢንስቲትዩት (ጋቪ) እና የክትባት ቅንጅት (ቫክሲን አሊየንስ) ይህ የክትባቶች መስተጓጎል እያስጨነቀን ነው፤ አንድ መፍትሄ እንፈልግ እያሉ ነው።

በአንድ በኩል ነፍስ እናድናለን እያልን በሌላ በኩል ነፍስ እያጠፋን ነው፤ የሚሉት ድርጅቶቹ ክትባት ይቁም የተባለበትን ሦስት አበይት ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።

አንዱ ወላጆች ለክትባት ብለው ከቤት ሲወጡ ቫይረሱ እንዳይዛቸው ስለሚሰጉ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ የጤና ባለሞያዎች በሙሉ ኃይላቸው እየተረባረቡ ያሉት ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት በመሆኑ ለሌሎች ክትባቶች ጊዜም ቦታም የላቸውም።

ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ክትባቶችን ወደ አገር ውስጥ ብሎም ወደ ጤና ጣቢያዎች ለማድረስ የጉዞ እቀባዎች በመኖራቸው ነው።

"ለምሳሌ ኩፍኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፤ ኮሌራም እንዲሁ" ይላሉ የዩኒሴፍ ዳይሬክተር ሄኔሪታ ፎሬ።

"ይህ ሌላ ያላሰብነው ጥልፍልፍ ችግር ይዞብን ይመጠል። እነዚህ አሁን እያንሰራሩ ያሉ የሕጻናት በሽታዎች ዓለም የተቆጣጠራቸው በሽታዎች ነበሩ" ሲሉ አስታውሰው "አሁን ከፍተኛው ስጋት፤ በጥሩ ሁኔታ ሥርጭታቸው ተገትቶ የነበረውና በመጥፋት ላይ የነበሩ በሽታዎች ዳግም የማንሰራራት ዕድል ማግኘታቸው ነው" ብለዋል።

ለምሳሌ በኒጀር ከአንድ ሺህ ሰዎች በላይ በኮቪድ-19 ተይዘዋል። በዋና ከተማዋ ወትሮ በወላጆችና ልጆች ጢም ብሎ ይሞላ የነበረ ጤና ጣቢያ ባዶውን በጸጥታ ተውጧል።

ይህም ወረርሽኙ የፈጠረው ፍርሃት ነው። መደበኛ ክትባት መቋረጡን ተከትሎ አካል ጉዳትን ብሎም ሞትን የሚያስከትለው ፖሊዮ በዚያች አገር እያንሰራራ ነው።

በጥቅምት ወር ብቻ ፖሊዮ በ4 ኒጀራዊያን ህጻናት ላይ ተመዝግቧል። ይህ ለኒጀርም ለዓለምም መልካም ዜና አይደለም።

80 ሚሊዮን ሕጸናት ክትባት አምልጧቸዋል

ወትሮ ይሰጡ የነበሩ መደበኛ ክትባቶች በኮቪድ-19 ምክንያት በመስተጓጎላቻ በደቡብ ምሥራቅ እሲያ 34.8 ሚሊዮን፣ በአፍሪካ 22.9 ሚሊዮን ሕጻናት ክትባት አምልጧቸዋል።

በኔፓልና በካምቦዲያ ኩፍኝ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ኮሌራ፣ ቢጫ ወባና ኩፍኝ ወረርሽኞች ማንሰራራታቸው ተመለክቷል።

የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የኅብረተሰብ ጤና ማዕከል ባጠናው ጥናት እነዚህ መደበኛ ክትባቶች በመስተጓጎላቸው በዓለም በየቀኑ 6 ሺህ ሕጻናት እየሞቱ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት የክትባት ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ ኬቲ ኦብራያን እንደተናገሩት እየከሰሙ የነበሩ በሽታዎች አሁን ዳግም እንዳያንሰራሩ ፍርሃት ገብቶናል ብለዋል። "በሽታዎቹ አንዴ ማንሰራራት ከጀመሩ በመላው ዓለም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የልጆች ሞት ይመዘገባል" ብለዋል።

ዳይሬክተሯ ኬቲ እንደሚሉት ይህ ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል፤ የመንግሥታት ትብብርና ቁርጠኝነት ካለ።

ይህ ከመደበኛ ክትባቶች መስተጓጎል ጋር ተያይዞ የተደቀነው ስጋት ለውይይት የቀረበው የዓለም መንግሥታት ትናንት ሐሙስ የዓለም የክትባት ቀንን በማመልከት በቪዲዮ በተበሰቡበት ወቅት ነው። የስብሰባው አሰናጅ ዩናይትድ ኪንግደም ነበረች።

በዚህ ስብሰባ ማጠቃለያ ሀብታም አገራት እና በጎ አድራጊዎች በድምሩ 7.4 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ እንዲለግሱ ይጠበቃል። ይህም እነ ጋቪ እና ቫክሲን አሊያንስ ያሉ ድርጅቶች ወሳኝ ክትባቶችን ለድሀ አገራት ሳያቋርጡ እንዲያቀርቡ ለማስቻል ይረዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ስብሰባ በድሀ አገራት መደበኛ ክትባቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ እንዴት ሊሰጡ ይገባል ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ያቀረበው ቁልጭ ያለ መፍትሄ የለም።