"ትራምፕ አሜሪካንን እየከፋፈሏት ነው" የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር

ጄነራል ጄምስ ማቲስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ጄምስ ማቲስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር
ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ማቲስ ያልተጠበቀና የሰላ ትችት በዶናልድ ትራምፕ ላይ ሰንዝረዋል።

"ዶናልድ በሥልጣኑ እየባለገ ነው፣ አሜሪካዊያንን አንድ አድርጎ ሊመራ ሲገባ እርሱ ግን እየከፋፈለን ነው" ብለዋል።

እምብዛምም ባልተለመደ ሁኔታ ሰነዘሩት በተባለ የሰላ ትችት የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ጄምስ ማቲስ "ከዶናልድ ትራምፕ በሳል አመራር መጠበቅ የዋህነት ነው" ብለዋል።

ጄኔራሉ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ለማርገብ ዶናልድ ትራምፕ የሄዱበት መንገድ አስቆጥቷቸዋል።

ጄኔራል ጄምስ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2018 የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡት አሜሪካ ጦሯን ከሶሪያ ምድር እንድታስወጣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድንገተኛ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን በመቃወም ነበር።

ከዚያ ጊዜ በኋላ በፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲህ በአደባባይ የሰላ ሂስ ሰንዝረው አያውቁም ነበር።

ትናንት ረቡዕ ግን እጅግ የሰላ የተባለውን ሂስ በአትላንቲክ መጽሔት ላይ በማሳተማቸው ጄኔራሉ ዳግም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆነዋል።

ሙገሳን እንጂ ሂስና መተቸትን ፈጽሞ የማይወዱት ዶናልድ ትራምፕ የጄኔራሉን የሰላ ሂስ ተከትሎ እርሳቸውም ብዕራቸውን ስለው ወደ ትዊተር ሰሌዳቸው ብቅ ብለው ነበር። የሚከተለውንም ምላሽ ሰጥተዋል።

"ይሄ ጄምስ ማቲስ የሚባል ጄኔራል ተብዬ በአሜሪካ ምድር እንዲሁ ያላግባብ የተጋነነ ስም የተሰጠው ጄኔራል ነው። እኔና ባራክ ኦባማን አንድ የሚያደርገን ነገር የለም መቼም፤ ካለ ግን እሱም የሚሆነው ጄኔራል ጄምስ ማቲስን ከሥራ ማባረራችን ነው። የእርሱ ቅጽል ስም "አባ በጥብጤ" ነው፤ ይህ ስም ሲያንሰው ነው። እኔ ቅጽል ስም ስጠው ብባል ግን "እብድ ውሻ" እለው ነበር።"

ጄኔራል ጄምስ ማቲስ በዶናልድ ትራምፕ ላይ በሰጡት ተጨማሪ ሂስ "በሕይወት ዘመኔ የአሜሪካንን ሕዝብ ለመከፋፈል እንጂ አንድ ለማድረግ ያልሰራ መሪ ቢኖር ዶናልድ ነው፤ አለመስራቱ ሳይሆን የሚገርመኝ አለመሞከሩም ጭምር ነው። ከዚያ ይልቅ ሊከፋፍለን ቀን ተሌት ይሰራል" ብለዋል።

"እነሆ ሦስት ዓመት ሊከፋፍለን ሞክሮ ውጤቱን እያየነው ነው። የሦስት ዓመታትን በሳል አመራር ማጣት ያመጣውን ገፈት መቅመስ ጀምረናል" ሲሉ ጄኔራሉ ጨምረው ተናግረዋል።

የቀድመው የመከላከያ ሚኒስትር ጄምስ ማቲስ በሂሳቸው መጨረሻ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ መከላከያ ሠራዊትን በሕዝባቸው ላይ ለማዝመት መዛታቸውን "እብደት" ብለውታል።

"መከላከያ ሠራዊታችን የራሱን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ ተቃውሞ የማድረግ መብቱን ለመገርሰስ ይሰማራል ብዬ በሕልሜም አስቤ አላውቅም፡፡. . . የታጠቀ ሠራዊትን ተቃውሞ ለወጣ ሕዝብ ማሰራመት ሕዝቡንና ሠራዊቱን ማቃቃር ነው የሚሆነው" ሲሉ ሂሳቸውን ቋጭተዋል።