የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሙስና ክስ ችሎት ፊት ሊቀርቡ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በሙስና ክስ በዛሬው ዕለት ግንቦት 16፣ 2012ዓ.ም ችሎት ፊት እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
በአገሪቷ ታሪክ አገሪቷን እያስተዳደረ ያለ መንግሥት ችሎት ፊት ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእየሩሳሌም ፍርድ ቤት በሚካሄደው የችሎቱ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስ የተመሰረተባቸው በጉቦ፣ በማጭበበር እና በእምነት ማጉደል ወንጀል ሲሆን፤ እርሳቸው ግን ክሱን በጥብቅ ተቃውመውታል፡፡
የ70 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የክሱ ሁኔታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተፎካካሪዎች ከሥልጣን እንዲወርዱ ያቀረቡትን ጥሪ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችሎት ፊት የሚቀርቡትም የብሄራዊ አንድነት መንግሥት ሆነው ከተሾሙ ከሳምንት በኋላ ነው፡፡
የእርሳቸው የፖለቲካ ተቀናቃኝ ቤኒ ጋንትዝም በአንድ ዓመት ውስጥ የተካሄዱ ግልጽ ያልሆኑ ምርጫዎችን ተከትሎ ሥልጣን ለመጋራት ተስማምተዋል፡፡
የቀኝ ክንፍ ሊኩድ ፓርቲ መሪ ቤንያሚን ኔታንያሁ ለረዥም ጊዜ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ነው፡፡ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2009 አንስቶ ሥልጣን ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከጎርጎሮሳዊያኑ 1996-1999 ድረስም ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ቤንያሚን የተከሰሱት በምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስተር ቤኒያሚን ኔታንያሁ 1,000፣ 2,000 and 4,000 በመባል በሚታወቁት ሶስት የክስ መዝገቦች ነው የተከሰሱት፡፡
- 1,000 የክስ መዝገብ የማጭበርበርና የእምነት ማጉደል ክስ፡ የተከሰሱትም በዋናነት ሲጋራዎችን፣ ሻምፓኝ እና ስጦታዎችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ የንግድ ሰዎች በመቀበላቸው ሲሆን ይህም ስልጣናቸውን በመጠቀም ላደረጉት ውለታ ምላሽ ነው ተብሏል።
- 2,000 የክስ መዝገብ የማጭበርበርና የእምነት ማጉደል ክስ፡ ዬዲዮት አሀሮኖት የተባለዉን የእስራኤል ጋዜጣ ስለሳቸው አዎንታዊ መረጃ ካሰራጨ እርሳቸውም በምላሹ የጋዜጣውን ህትመት ስርጭት ብዛት ለመጨመር ተደራድረዋል።
- 4,000 የክስ መዝገብ በጉቦ፣ ማጭበርበር እና የእምነት ማጉደል፡ ድርጊቱ ሲፈጸም ጠቅላይ ሚኒስትርና የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የነበሩት ኔታንያሁ፤ የቤዜቅ ቴሌኮም ኩባንያ የአክሲዎን ባለድርሻ የሆኑት ሻኡል ኢሎቪችን ለመጥቀም የቁጥጥር ሕጎችን በማስፋት ነው የተከሰሱት፤ ይህም በኢሎቪች ዋላ የዜና ገጽ ላይ አወንታዊ ሽፋን ለማግኘት የተደረገ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ "በፖለቲካ ተቃዋሚዎች የተሰነዘረ የስም ማጥፋት ሴራ ነው" ሲሉ ሁሉንም ክሶችን አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡
ቤንያሚን ናታንያሁ በእስራኤል ታሪክ ረዥም ጊዜ በሥልጣን የቆዩ መሪ ናቸው።












